ሚኒስቴሩ ከ400 በላይ ተጠርጣሪዎች እጃቸውን በሰላም መስጠታቸውን አስታወቀ

በአንዳንድ የሀገሪቱ አከባቢዎች ተፈጥሮ የነበረው ሁከትና ብጥብጥ ለሙሉ ለሙሉ በመቆሙ  አስተማማኝ ሰላም መስፈኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ስክሬታሪያትና የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ ፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኮማንድ ፖስቱ ባሁኑ ወቅት በሀገራችን ተፈጥሮ የነበረውን አለመረጋጋትና ሁከትን ማስቆም የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል ፡፡

በሀገሪቱ የተለያዩ ጫፎች በሰላም እንዳይንቀሳቀሱ ተደርገው የነበሩ ዋና ዋና የመንገድ አውታሮችና ቀጠናዎች ላይ ሰላማዊ የሆነ እንቅስቃሴ እንዲኖር ሰፊ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል ፡፡

በሁከትና በብጥብጥ የተሳተፉ ከ400 በላይ ተጠርጣሪዎች የ10 ቀን ገደቡ ከማለፉ በፊት በራሳቸው እጃቸውን መስጠታቸውን ነው ያስታወቁት ፡፡

እንደዚሁም ሚኒስትሩ በየአከባቢው ተዘርፈው የነበሩ ከ1ሺ 500 በላይ ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል ፡፡

በሀገሪቱ ጠረፍ ነባር ኬላዎችን በማጠናከርና አዳዲሶችን በመጨመር የጸረ ሰላም ሃይሎች እንቅስቃሴ እንዳይኖር መከላከል መቻሉን አስረድተዋል ፡፡

ጸረ- ሰላም ኃይሎች የሚያሻግሯቸውን የገንዘብና የትጥቅ መሳሪያዎችም በመያዝ ከውስጥም ከውጭም እንዳይወጡና እንዳይገቡ በማድረግ በሀገራችን ውስጥ አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር ሰፊ ስራ መሰራቱን አብራርተዋል ፡፡

በየአከባቢው ህብረተሰብ በስፋት እንዲሳተፍ በማድረግ በሁከት የተሳተፉ አካላትን ለጸጥታ አካላት እያስረከበ መሆኑን አመልክተዋል ፡፡

አቶ ስራጅ በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል ፍንፍኔ ዙሪያ፣ ሰሜን ሽዋ፣ ምስራቅ ሸዋ የተያዙት ተጠርጣሪዎች በአዋሽ ማሰልጠኛ ማዕከል እንደሚገኙ አስታውቀዋል ፡፡

በምስራቅና ምዕራብ ጉጂ፣ ባሌ ጨምሮ በምስራቅና ምዕራብ ሃረርጌ  የተያዙ በዝዋይ አላጌ ማሰልጠኛ ማዕከል የሚቆዩበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል ፡፡

በቆላው ወለጋ፣ በምዕራብና በምስራቅ አሩሲ ዞኖች እንዲሁም ምዕራብ ሸዋ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች የተያዙ ደግሞ ጦላይ አከባቢ ይቆያሉ ነው ያሉት ፡፡

በአማራ ክልል በሰሜን እና በደቡብ ጎንደር፣ ውስን በአዊ ዞንና በምዕራብ ጎጃም፣ በጎንደር ከተማና በባህርዳር ከተማ የተያዙ ተሃድሶአቸውን የሚወስዱት በባህዳር ከተማ ይሆናል ብለዋል ፡፡

በደቡብ ክልል በጌዴኦ ዞን የተፈጠረው ችግር ጋር የተያዙ ደግሞ በይርጋዓለም ከተማ እንደሚገኙ ገልጸዋል ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ተጠርጥረው የተያዙ የህግ ታራሚዎችም በአዲስ አበባ ስልጠና ይገኛሉ ነው ያሉት ፡፡

በአጠቃላይ የተያዙ ተጠርጣሪዎች አሁን ተሰባስበው የገቡ በመሆናቸው ቀጣይ በዝርዝር በስልክም ይሁን በሌላ አግባብ ከቤተሰቦቻቸው የሚገናኙበትን ሁኔታ አመቻችተው በቅርቡ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል ፡፡

እስካሁንም ከ2ሺ በላይ ሽማግሌዎችና ፋብሪካዎች ጭምር ሲያቃጥሉ የነበሩ ከ18 ዓመት በታች ታዳጊ ተጠርጣሪዎች ደግሞ ምክር ተሰጥቶአቸው እንዲወጡ መደረጉን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል ፡፡

በሚደረጉ ፍተሻዎች ላይ እስካሁን በተደረገው ክትትልና ቁጥጥር መሰረት እስከ 4 የሆኑ የፖሊስ አካላት በድርጊቱ ተሰማርተዋል ተብለው በጥቆማ መያዛቸውን ጠቁመዋል፡፡

በኦሮሚያና በአዲስ አበባ አከባቢ የጸጥታ አካላት ሳይሆኑ መስለው የተሰማሩ ግለሰቦችም በህዝብ ጥቆማ ተይዘው በህግ አግባብ እየተጣሩ መሆኑን አስታውቀዋል  ፡፡

ባንጻሩ በአንዳንድ የኦሮሚያ አከባቢዎችና በአዲስ አበባ ከተማ ሰዎችን ለማጥቃት የውሸት ጥቆማ የሰጡ ግለሰቦችም ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አስታውቀዋል ፡፡

በሌላም በኩል ህብረተሰቡ በየአከባቢው የወደሙ የመንግስት፣ የግል ተቋማትና የግለሰቦች መኖሪያቤተችም ጨምሮ በራሱ ዓቅም የገነባበት ሁኔታ መኖሩን አቶ ሲራጅ ገልጸዋል ፡፡

በአንዳንድ ከተሞች ተቋርጦ የነበረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችም አሁን ህብረተሰቡ የተለመደ ዕለታዊ ስራው በሰላም እያካሄደ መሆኑን አንስተዋል፡፡

አሁን የተፈጠረው ብጥብጥ ዳግም እንዳይከሰት ህዝቡ በንቃት የተሳተፈበት ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል ፡፡

አቶ ሲራጅ ከአዋጁ በኋላ በአገር ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው ሁከት፣ የመሰረተ ልማቶች ውድመትና የሰው ህይወት መጥፋት አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም ማድረግ መቻሉ ትልቅ ስኬት መሆኑን አስገንዝበዋል ፡፡

አዋጁ ያሰፈለገበት ምክንያትም በአገራችን ተፈጥሮ የነበረውን አለመረጋጋት ተከትሎ በመደበኛው የህግ አግባብ መንግስት ተገቢውን ምላሽ መስጠት ባለመቻሉ የህዝቦች ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ታሳቢ ተደርጎ እንደነበር ማስታወሳቸውን የዘገበው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ነው፡፡