ህዝቡን በሀቀኝነትና በታማኝነት ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ተሿሚ ሚኒስትሮች ገለጹ

አዲስ የተሾሙት የካቢኔ አባላት የተረከቡትን ኃላፊነት በብቃትና በጥራት በመወጣት ህዝብን በሀቀኝነትና በታማኝነት ለማገልገል ቆርጠው መነሳታቸውን ገለጹ፡፡

ዋልታ ካነጋገራቸው አዲስ ተሿሚዎች መካከል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ኃላፊነቱ ህዝብና አገርን በታማኝነት ለማገልገል የተሰጠ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡

በመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ለዜጎችና ለአገር ዕድገት የሚጠቅሙ አሰራሮች ለመዘርጋት እንደሚሰሩ ዶክተር ነገሪ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ መገናኛ ብዙኃን የለውጥ ሞተር ናቸው›› ያሉት ሚኒስትሩ  ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን በመጠቀም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለተሻለ ለውጥ እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን በሚኒስትርነት ለመምራት የተሾሙት ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም ኃላፊነቱ ትልቅ ደስታን እንደፈጠረባቸው ነው ያመለከቱት፡፡

‹‹ህዝብና አገርን በታማኝነትና በቁርጠኝነት ማገልገልን የመሰለ ደስታ የለም›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

በተመደቡበት የአመራርነት ቦታ ላይ የኢትዮጵያን ገፅታ የሚገነቡ፣ የቱሪዝም ዘርፉን የሚያጠናክሩና የገቢ ምንጭን ለማሳግ የሚረዱ ተግባራትን በማከናወን አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡

የማህፀንና የፅንስ ስፔሻሊስት የሆኑት ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነ የጤና ጥበቃ ሚኒስትርነቱን የአመራርነት ቦታ በመረከባቸው የጤናውን ዘርፍ በተሻለ ብቃትና ቁርጠኝነት በመምራት ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ ተግተው እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡

ዜጎች ጤናቸው ተጠብቆ አምራች ሆነው ለህዝባቸውና አገራቸው ዕድገትና ብልፅግና እንዲሰሩ የተጀመረው ጥረት በስኬት እንዲታጀብ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚያበረክቱ አስገንዝበዋል፡፡

አዲሱ የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዶክተር ገመዶ ዳሌ በበኩላቸው አገሪቱ የነደፈችው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ስትራቴጂው ዕውን እንዲሆን ጠንክረው እንደሚሰሩ ይገልፃሉ፡፡

ህዝብና መንግስት የጣለባቸውን ትልቅ ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡

አካባቢን ከመራቆት በመታደግ፣ ደንን በመንከባከብና በመጠበቅ የዓለም ስጋት የሆነው የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ለሚያስችሉ ተግባራት ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩም አስገንዝበዋል፡፡

አዳዲሶቹ ሚኒስትሮች ዕውቀትና ልምዳቸውን ተጠቅመው የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የአገሪቷን ዕድገት ለማፋጠን ጠንክረው እንደሚሰሩ  አረጋግጠዋል፡፡

ከመልካም አስተዳደር እጥረት ጋር በተያያዘ የሚነሱ የህዝብ ቅሬታዎችን ለመፍታትም የበኩላቸውን ጥረት እንደሚደርጉ ነው ያመለከቱት፡፡