ለሁሉም የሚያገለግል የቴሌቭዥን ማሰራጫ ጣቢያ ሊቋቋም ነው

ሁሉንም የቴሌቭዥን ጣቢያዎች የሚያገለግል የጋራ የቴሌቭዥን ማሰራጫ ጣቢያ ሊቋቋም መሆኑ ተመለከተ፡፡

አዲስ የሚቋቋመው የቴሌቭዥን ማሰራጫ ጣቢያ በአገሪቱ ውስጥ ለሚገኙ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች የጋራ ማሰራጫ ሆኖ እንደሚያገለግል የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ለዋልታ አስታውቋል፡፡

የማሰራጫ ጣቢያው የቴሌቭዥን ብሮድካስተሮች የማሰራጫ ጣቢያ መገንባት ሳያስፈልጋቸው የብሮድካስት ፈቃድ በማውጣት ቻናል በመከራየት የሚሰሩበትን ዕድል እንደሚፈጥር በባለሥልጣኑ የዕቅድና ማስታወቂያ ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡

‹‹የቴሌቭዥን አገልግሎቱ ከአናሎግ ወደ ዲጂታል እየተሸጋገረ ነው›› ያሉት አቶ ግዛው አዲስ የሚገነባው ማሰራጫ ጣቢያ የዲጂታል ሽግግሩን ለማሳለጥም የጎላ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡ አሁን በሳተላይት ላይ የሚተላለፉ የተለያዩ የቴሌቭዥን ስርጭት ዓይነት አገልግሎት መስጠት የሚችል ነው፡፡

የቴሌቭዥን ማሰራጫ ጣያ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ግዛው በቴሌቭዥን ስርጭት ዘርፍ የሚሰማሩ አካላት ለጣቢያ ግንባታ የሚያወጡትን ከፍተኛ ወጭ እንደሚያስቀር አስገንዝበዋል፡፡

አቶ ግዛው እንዳሉት የማሰራጫ ጣቢያው ከ22 በላይ ቻናሎች ይኖሩታል፡፡ በርካታ ብሮድካስተሮችን ማስተናገድ ይችላል፡፡  የቴሌቭዥን ብሮድካስተሮች ይዘቱን ብቻ በማዘጋጀት አገልግሎቱን አየር ላይ የሚያውሉበት ቀላል አሰራር ይዘረጋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሁሉም የቴሌቭዥን ጣቢያዎች የማሰራጫ ጣቢያ ቢገነቡ ሁሉንም ቻናሎች የሚጠቀምበት ስለማይኖር ብክነት ከመሆን ያለፈ ፋይዳ የለውም ብለዋል፡፡

የጋራ ማሰራጫ ጣቢያ በተለያዩ አገራት ተግባራዊ መደረጉን ዳይሬክተሩ ጠቁመው እነ ደቡብ አፍሪካ ይህን ሥርዓት በመገንባት ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የመንግስት የልማት ድርጅት የሆነውን የማሰራጫ ጣቢያ ለማቋቋም ደንብ እየተዘጋጀ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ በአዲስ መልክ ይፀድቃል ተብሎ የሚጠበቀው የብሮድካስት አዋጅም አዲሱን አሰራርና የአገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥ ለማሳለጥ የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

የማሰራጫ ጣቢያው የመሰረተ ልማት ግንባታ በኢትዮጵያ የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጄንሲ እየተከናወነ መሆኑ ከባለሥልጣኑ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

የማሰራጫ ጣቢያው ተቋቁሞ ለአገልግሎት ሲበቃ የብሮድካስት ፍቃድ ያገኙ ተቋማት ከጣቢያው ጋር ውል በማሰር ቻናል በመከራየት ይሰራሉ፡፡