በኢትዮጵያ መንግስት እና በኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ግንባር መካከል የሰላም ስምምነት ተፈረመ

በኢትዮጵያ መንግስት እና በኢትዮጵያ  አንድነት አርበኞች ግንባር መካከል የሰላም ስምምነት ተፈረመ።

ግንባሩ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ከመንግስት ጋር የተለያዩ ውይይቶችን አድርጎ የትጥቅ ትግል አማራጩን በመተው በሰላማዊ መንገድ ለመታገልና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በመቀበል ለመንቀሳቀስ እና ለኢትዮጵያ ሔራዊ ጥቅም ለመቆም መወሰኑን ገልጿል።

ስምንት ነጥቦች ያሉት የሰላም ስምምነትም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተፈራርሟል።

የመከላከያ ሚንስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በትጥቅ ትግል ውስጥ የነበሩ የተለያዩ ድርጅቶችና ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ እየገቡ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ግንባርም የዚሁ አካል መሆኑን አስረድተዋል ።

 መንግስት የትጥቅ ትግል አማራጭን በመተው በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ የሚፈልጉ አካላትን ለመቀበል ሁሌም ዝግጁ መሆኑንም የመከላከያ ሚንስትሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ግንባር ሊቀመንበር አቶ ቱዋት ፖል ቻይ ከጦርነት ምንም የሚገኝ ነገር ስለሌለ ወደ ሰላማዊ አማራጭ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ለሰላማዊ ትግል የተመቸ በመሆኑ አባሎቻቸውን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት በሰላማዊ መንገድ እንደሚታገሉም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ግንባር የኢፌዲሪን ሕገመንግስት በመጻረር የትጥቅ ትግልን አማራጭ አድርጎ ሲታገል መቆየቱ ይታወቃል (ኢብኮ)።