ኢትዮጵያ ተከባብሮ በመኖር ባህል ለዓለም ተምሳሌት የሆነች አገር ናት-አቶ ሙሉጌታ ውለታው

ኢትዮጵያ  ተከባብሮ የመኖር  ባህልን በማጉልበት ለዓለም ተምሳሌት የሆነች ድንቅ አገር  መሆኗን የፌደራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር አካባቢ ልማት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሙሉጌታ ውለታው ገለጹ ።

አቶ  ሙሉጌታ ከዋልታ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም የተለያዩ እምነት ተከታዮች የሚገኙባት አገር ሆና ለዘመናት  በጋራ  ተከባብሮ የመኖርን እሴት በመጠበቅ የኖረች አገር መሆኗን  ገልጸዋል ።

እንደ አቶ ሙሉጌታ ገለጻ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ብዝሃነትን በማስተናገድና ዴሞክራሲያዊ የፌደራላዊ ሥርዓትን ተግባራዊ በማድረግ አንዱ ከሌላው ጋር በእኩልነት እንዲኖር እንዲሁም የሚያጋጥሙ ግጭቶችን እንዲፈቱ በማድረግ የሰላም እሴት እንዲጎለብት የተለያዩ ጥረቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ ብለዋል  ።

በአገሪቱ የሰላም እሴትን ይበልጥ ለመገንባት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው የተለያዩ መድረኮችንና የኃይማኖት ተቋማትን በመጠቀም ቀጣዩ ትውልድ ልዩነቶችም ቢኖሩት   በውይይት የመፍታት ባህልን እንዲያካብት የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመቀናጀት ሲካሄድ መቆየቱን አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል።

በአገሪቱ  የሰላም  ባህል እንዳይጎለብት ከሚያደርጉ እንቅፋቶች መካከል በኃይማኖት ሽፋን የሚካሄዱ የአክራሪነትና ጽንፈኝነት ተግባራት መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ሙሉጌታ  የአክራሪነትና ጽንፈኝነት የሚመነጩት ከሓይማኖታዊና ህገመንግሥታዊ እውቀት ማነስ  በመሆኑ መንግሥት በቀጣይ ሊሠራበት ይገባል ብለዋል ።

በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ከውሃ ፣መሬትና ድንበር  ጋር ተያይዘው በተለይ በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚከሰቱ ግጭቶችን  ለመፍታት በተደረጉት ጥረቶች ስኬቶች   መመዘግባቸው  የሚናገሩት  አቶ ሙሉጌታ በአፋርና በኢሳ ጎሳዎች ፣ በደቡብና በኦሮሚያ ፣ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል፣ በኦሮሚያ ሶማሌ አጎራባች አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ ግጭቶች በአብዛኛው ተፈትዋል ብለዋል ።

በኢፌዴሪ  ህገ መንግሥት እንደተደነገገው  ዘላቂ ሰላምን በአገሪቱ ማስፈን ከአራቱ ዋና ዋና አጀንዳዎች  መካከል  ሲሆን ድህነትን  በማስወገድና የህልውና  ጉዳይ የሆነውን ዴሞክራሲን ባህልን በማጉልበት እንዲሁም የዴሞክራሲ ሥርዓትን በማጠናከር  በአገሪቱ ሰላም መረጋገጥ  እንደሚገባ  አቶ ሙሉጌታ  አመልክተዋል ።

የፌደራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር ልማት ሚኒስቴር የግጭት መከላከልና አፈታት ሥራውን ለወደፊቱ ይበልጥ ለማጠናከር አገራዊ  የግጭት መከላከልና አፈታት ስትራቴጂውን ለማሻሻል እየሠራ እንደሚገኝ  ዋልታ እንፎርሜሽን ማዕከል  ዘግቧል ።