ህወሓት የመንግስት ስልጣንን ለግል ጥምቅና ክብር መጠቀምን ለማስወገድ እንደሚሰራ አስታወቀ

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ከፍተኛ አመራሮች በመቐለ ከተማ ላለፉት ስምንት ቀናት ባደረጉት በጥልቅ የመታደስ ንቅናቄየመንግስት ስልጣንን ለህዝብ ጥቅም ከማዋል ይልቅ ለግል ጥምቅና ክብር መጠቀም የሁሉም ችግሮች ምንጭ መሆኑን አረጋግጧል ፡፡

ይህንን ለማሰወገድ እንደሚሰራም ነው ህወሓት በመግለጫው ያረጋገጠው

በተለይም የዴሞክራሲ ተቋማት ሊደርሱ በሚገባቸው ደረጃ ላይ አለመድረሳቸው እና በመልካም አስተዳደር እጦት ህዝብ ለምሬት መዳረጉ መግለጫው ጠቅሷል።

እነዚህ ሁኔታዎች በድርጅትና በህዝብ እንዲሁም በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለው መተማመን እንዲሸረሸር አድርጓል ነው ያለው ።

ህወሓት ኪራይ ሰብሳነትን ለማጥፋት ተከታታይ ትግል አለማድረግ፣ የፀረ ዴሞክራሲ አመለካከት እና ተግባር፣ የውስጠ ድርጅት ትግል መቀነስ፣ አድርባይነት እና ብልሹ አሰራር መኖራቸውን በግምገማው አረጋግጧል

እነዚሁም በክልሉ የተለያዩ ግንባሮች የተመዘገቡትን ድሎች የሚያደበዝዙ እና በድርጅቱ ውስጥ የነበሩትን የውስጠ ድርጅት ትግል የሚያቀዝቅዙ ድክመቶች መሆናቸውን ነው ያስገነዘበው ፡፡

ስልጣን ለህዝብ ጥቅምና አገልግሎት ከመዋል ይልቅ ለግል ጥቅምና መገልገያነት መጠቀም ለሁሉም ችግሮች መነሻ በመሆኑም አመራሮቹ እንደሚታገሉ ነው ያረጋገጡት።

የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ለማጎልበት እና በመንግስት የስራ ኃላፊዎች ላይ የሚካሄደውን ክትትልና ቁጥጥር ለማጠናከር ምክር ቤቶች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የደረጋል ነው ያለው።

በተጨማሪም የሲቪክ ማሀበራት፣ የመገናኛ ብዙሃን እና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱም እንደሚሰራ አረጋግጧል

የተጀመረው የተሃድሶ ንቅናቄ ወደ ህዝቡ እንደሚወርድ ያመለከተው መግለጫቸው፤ ህዝቡም ያለምህረት ለመግምገምና ለማረም በንቅናቄው እንዲሳተፍ ከፍተኛ አመራሮቹ ጥሪ አቅርበዋል።

ህወሓት በመግለጫው ባለፉት 15 ዓመታት የተመዘገቡ ዓበይት ስኬቶችም አንስቷል ።

በክልሉ በ1991 ዓመተ ምህረት 56 በመቶ ነበረው ከድህነት ወለል በታች የሚኖር ህዝብ በ2007 ወደ 23 በመቶ መውረዱ ነው የጠቀሰው።

በተለይ የወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥም የድህት ቅነሳ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም በመግለጫቸው ላይ አስታውቀዋል።

በክልሉ 4ሺ ሄክታር ብቻ የነበረው የመስኖ ልማት አሁን ወደ 270 ሺ ሄክታር መድረሱ ነው ያረጋጠው ፡፡

በአፈርና ውሃ ጥበቃ የተከናወነው አመርቂ ውጤት በክልሉ ድርቅለመቃቋም የሚያስችል  እርሻ ምቹ ዕድል መፈጠሩን መግለጫው አመልክቷል ፡፡

ህወሓት በስብሰባው የህዳሴ ጉዞ፣ በድርጅቱ ላይ የተጋረጡ አደጋዎችና ፈተናዎች፣ የህወሓት የስራ አስፈፃሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ ግምገማ እና ቀጣይ የትግል አቅጣጫ የሚሉ ነጥቦች ላይ ሰፊ ግምገማ ማካሄዱን መግለጫው ጠቁሟል ።