የፐብሊክ ሰርቪሱ መሪ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ለሚመለከታቸው አካላት ተሠራጭቷል

በአገሪቱ  የፐብሊክ ሰርቪሱ የሚመራበት ዝርዝር መሪ ዕቅድ ተዘጋጅቶ በፌደራልና በክልል ደረጃ  ለሚገኙ  አካላት  መሠራጨቱን  የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃይል ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ ።

በፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃይል ልማት ሚኒስቴር የመልካም አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ተመስገን ጥላሁን ለዋልታ እንደገለጹት በዘንድሮ ዓመት በአገር ደረጃ የለውጥ ሂደቱን  ለማቀጣጣል የሚያስችል የመሪ ዕቅድ ሰነድ ለፌደራል ተቋማትና ለሁሉም ክልሎች በመላክ ለተግባራዊነቱ እንዲንቀሳቀሱ ጥረቶች እየተካሄዱ ይገኛል ብለዋል ።

የመሪ ዕቅዱ የቢኤስ ሲ የለውጥ  ሂደትን መሠረት ያደረገ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ተመስገን ዕቅዱ የሪፎርም ሂደት ፣ የመልካም አስተዳደርና የሰው ሃብት የአደረጃጃትና የሬጉላቶሪ ሥራዎችን  በበላይነት  ለመምራት  የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል ።

ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ የወጣው የመሪ ዕቅድ ላይ ሁሉም አካላት ግንዛቤ እንዲዙበት  ከተደረገ በኋላ የሪፎረሙና የመልካም አስተዳደር ለውጦቹ በአግባቡ ተግባራዊ ስለ መደረጋቸው   ድጋፍና ክትትል  የሚደረግ  መሆኑን አቶ ተመስገን አስረድተዋል።

በተለይ የመልካም  አስተዳደርና የሪፎርም  ጉድለት  በተስተዋለባቸው ተቋማት ላይ ግምገማ በማካሄድ አስፈላጊ  ድጋፍ  እንደሚደረግ  የገለጹት  አቶ ተመስገን በሚደረገው የክትትልና ድጋፍ መሠረት የትኛውም የፐብሊክ  ሰርቪስ ተቋም ያለበትን  የአፈጻጻም ደረጃ በዓመቱ መጨረሻ ላይ እንደሚቀመጥ አመልክተዋል ።

የፐብሊክ ሰርቪስ ተቋማትን ያሉባቸውን ክፍተት በመለየት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከአጫጭር ጀምሮ ረጃጅም የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን እንደሚያመቻች የሚናገሩት አቶ ተመስገን በተለይ  የኮሪያና የሲንጋፖር የለውጥ ተሞክሮን በመውሰድ ወደ አገሪቱ ሁኔታ በማምጣት ሪፎርምን  ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አቅምን ለመገንባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል ።

የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኛው በሥራው ውጤቱ እንዲበረታታ ለማድረግ የአሠራር  መመሪያዎች ተዘጋጅተው ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ዝግጅቶች ተካሄደዋል ያሉት አቶ ተመስገን መመሪያው በሚኒስትሮች ምክርቤት ሲፀድቅ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀዋል ።

ከፐብሊክ ሰርቪሱ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ከዜጎች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ለማስተናገድ ሚኒስቴር  መሥሪያ ቤቱ የዜጎች ቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ ዳይሬክቶሪየት የሚል ክፍል  መከፈቱንና ዜጎች ያላቸውን ቅሬታዎችን በማቅረብ እየተስተናገዱ መሆኑን አቶ ተመስገን ጠቁመዋል ።

በመጨረሻም በአገሪቱ  የመልካም አስተዳደርማስፈንና ሪፎርም ተግባራዊ ማድረግ  የህልውና ጉዳይ  በመሆናቸው  ዜጎች  የነቃ ተሳትፎ  በማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡ  ጥሪ አቅርበዋል ።