ኮማንድ ፖስቱ ሁለት ዕገዳዎች ማንሳቱን አስታወቀ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ያልተፈቀዱ አልባሳትን እና የዲፕሎማቶች እንቅስቃሴን የሚገድቡ ዕገዳዎችን ሲያነሳ ሌሎች በጸጥታ ኃይሎች የሚወሰዱ እርምጃዎችን ማሻሻሉን አስታወቀ ፡፡

የኮማንድ ፖስቱ ሰክሬታሪያትና የመከላከያ ሚኒስቴር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ያልተፈቀዱ አልባሳትን መልበስ አስመልክቶ የህግ አስከባሪ ኃይሎችን ዩኒፎርም ይዞ መገኘት ወይም በቤት ውስጥ ማስቀመጥን የተደረገው ክልከላ ከዛሬ ጀምሮ መነሳቱን አስታውቀዋል ፡፡

ይህም የሆነው በመላ ሀገሪቱ በተለይም በገጠሩ ህብረተሰብ የመከላከያ ሰራዊት አልባሳት በስፋት የሚገኙ በመሆናቸው አልባሳቱ ይዞ መገኘትንና  ቤት ውስጥ ማስቀመጥ ክልከላው እንዲቀር ከህዝብ ጋ በተደረገው ውይይት ኮማንድ ፖስቱ በመስማማቱ እንዲነሳ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

ይሁንና የአስቸካይ ጊዜ አዋጁ እስኪያበቃ ድረስ አልባሳቱን መልበስ ፣ለሌላ ሰው አሳልፎ መስጠትና መሸጥ በሚል የተደነገገው ክልከላ አሁንም እንዳልተነሳ ነው ያስገነዘቡት ፡፡

የኮማንድ ፖስቱ ዕውቅናና ፈቃድ ሳያገኙ ዲፕሎማቶች ለራሳቸው ጥበቃ ሲባል ከ40 ኪሎ ሜትር ዙሪያ ውጭ እንዳይንቀሳቀሱ የተደረገው ክልከላም መነሳቱን ገልጸዋል ፡፡

የዚሁ ምክንያትም በአገሪቱ ተፈጥሮ የነበረው ሁከት ተወግዶ አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት በመስፈኑ መሆኑን ነው ያስረዱት ፡፡

እንደዚሁም በቱሪዝም ስፍራዎች ፣በኢንቨስትመንትና በሌሎችም የስራ መስኮች እየተንቀሳቀሱ ያሉት በርካታ የውጭ አገር ዜጎች ነጻነት ለመጠበቅና የሀገራችን መልካም ገጽታ ወደ ነበረበት ለመመለስ ሲባል መሆኑን አብራርተዋል ፡፡  

በሌላም በኩል ኮማንድ ፖስቱ እራስን ለመከላከል በህግ አስከባሪዎች ስለሚወሰድ የተሻሻለ እርምጃ ይፋ አድርገዋል ፡፡

በሕግ አስከባሪዎችና በድርጅቶች ጥበቃ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች አዋጁን ለማስፈጸም በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በጦር መሳሪያ ፣በስለት ፣በኃይል ወይም በሌላ ማናቸውም ዘዴ አማይነት በሕይወት፣በአካል እና በንብረት ከሚደርስ ጉዳት ለመከላከል የሚያስችል እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ ነው ያሉት ፡፡

ማንኛውም የህግ አስከባሪ አካል ፍተሻ ሲያደርግ ንብረቱን ለሚፈትሸው ሰው ፤የመስሪያቤቱን መታወቂያ የማሳየት ፣የመጣበትን ምክንያት የመግለጽ ፣የብርበራ ሂደቱን እንዲከታተል የመፍቀድ እና በብርበራው ወቅት የአከባቢውን ፖሊስ እና የህብረተሰብ አባላት በታዛቢነት እንዲገኙ የማድረግ ግዴታ እንዳለበት አስገንዝቧል ፡፡

ይህም የሆነበት ምክንያት አንዳንድ ግለሰቦች የህግ አስከባሪ አባላት በመምሰል ሲበረብሩ እየተገኙ በመሆናቸው መሆኑን ነው በመግለጫቸው ያመለከቱት ፡፡

ሌላው ማንኛውም የህግ አስከባሪ አካል ፍተሻውን ከማካሄዱ በፊትም ሆነ በኋላ የሚያገኛቸውን መረጃዎች ለሚመለከተው አካል ከመግለጽ ወጪ በሚስጢር የመያዝ ግዴታ እንዳለበት አቶ ሲራጅ አስታውቀዋል ፡፡

ዋልታ እንደዘገበው በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥልበት ሚኒስትሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል ፡፡