የኦህዴድ ጥልቅ ተሃድሶ ችግሮችን ነቅሶ ለማውጣትና ልማት ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው

የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦህዴድ/ እያካሄደ ያለው ጥልቅ ተሃድሶ ችግሮችን ነቅሶ ለማውጣትና ሕዝቡ ተስፋ የሚጥልበትን ልማት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ አስታወቁ።

በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ባለው የመካከለኛ አመራር ጥልቅ ተሃድሶ የውይይት መድረክ ላይ ሊቀመንበሩ እንደገለጹት በክልሉ የሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች በመፍታት የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ማጠናከር ይገባል።

"በጥልቅ ተሃድሶው ድርጅቱ ያለውን አሰራር፣ ጥንካሬና ድክመትን በመገምገም የህብረተሰቡንና የአካባበውን ነባራዊ ሁኔታ ለመረዳትና ከወቅቱ ሁኔታ ጋር እራሱን እያመዛዘነ ለማስተካከል እጅግ አስፈላጊና ተገቢ ነው "ብለዋል።

ድርጅቱ የመጀመሪያውን ተሃድሶ ሲያደርግ 15 ዓመታት ማስቆጠሩን ጠቆሙት አቶ ለማ በዚህ ጊዜ ውስጥ በርካታ ለውጦች መገኘታቸውን ተናግረዋል።

በእዚኒህ ዓመታት እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ቁጥር ታሳቢ በማድረግ በልማት ዘርፉ አንፀባራቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው "የወጡ ፖሊሲዎች፣ህጎችና የምንሰራቸው የየእለት ስራችን ከህዝብ ፍላጎት ጋር በማነፃፀር እንዲገመገሙ ይደረጋል" ብለዋል ።

ጥልቅ ተሃድሶው የህዝብን ጥቅም በማስከበር ረገድ ያሉ ጉድለቶችንና መልካም ነገሮችን በመመርመር መስተካከል የሚገባቸውን በዚሁ አግባብ ተፈጻሚ ለማድረግ ዓይነተኛ መሳሪያ ነው።

ባለፉት ሦስት አምስት ዓመታው በህብረተሰቡ ውስጥም በርካታ ለውጦች እንዳሉ የተናገሩት ሊቀመንበሩ የህዝብ የልማት ፍላጎት መጨመሩን፣የመንግስት ስራ መስፋቱንና ውስብስብ ከመሆኑ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር እየታየ የውስጥ አቅምን መለካት የተሃድሶው ዋነኛ ማጠንጠኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በመነሳት የህዝቡን ፍላጎት አሁን ያለው አቅም፣ ስፋትና ሀብት እንዲሁም የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስና ለማሳካት ድርጅቱ ራሱን ለመፈተሽ መዘጋጀቱ ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

የድርጅቱ ሊቀመንበር እንዳመለከቱት ከጥልቅ ተሃድሶው በፊት የተሰሩ ማህበራዊ፣ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ቢኖሩም በዚያው ልክ የሚታዩ ጉድለቶች ስላሉ ህብረተሰቡን ለቅሬታ ዳርገውታል፡

"ቅሬታው የተባላሹ ነገሮች እንዲስተካከሉለት ከመፈለግ የመነጨ በመሆኑ እንደ ድርጅትና እንደ መንግስት ተስተካክለን እንድንገኝ የሚያግዝ ነው "ብለዋል ።

ፍትህ በገንዘብ ሳይሆን በአግባቡ ለዜጋ እንዲሰጥ ከመፈለግ የመነጨ ቅሬታ በመሆኑ ድርጅቱ አንድ በአንድ ችግሮቹን ነቅሶ በማውጣት የማስተካከል እርምጃ እንደሚወስድ አቶ ለማ ተናግረዋል፡፡ 

ሥርዓቱን ለማስቀጠል የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋን እልባት መስጠት ተገቢ መሆኑን ጠቁመው " ሁላችንም ቆም ብለን ራሳችንን እያየን ልንፈትሽ ግድ ነው "ብለዋል።

ድርጅቱ አስፈላጊውን አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ ጭምር ለመውሰድ አቋም ወስዶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱንም አስታውቀዋል።

የህዝቡን ጥያቄ በጋራ በመነጋገርና በመመካከር ለመመለስ ታስቦ የተዘጋጀ ተሃድሶ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ለማ “እኛው በእኛው ህዝብ ላይ የፈጸምናቸውን በደሎች አመራሩ አንድ በአንድ እያነሳ ሂስና ግለ ሂስ ያደርጋል” ብለዋል።

"የጀመርነውን ተሃድሶ እስከ ታች በማውረድ ህብረተሰቡ ተሳታፊ እንዲሆን ካደረግን የገባንባቸው ችግሮች አስተካክለን የተሻለና ተስፋ ያለው ስራ እንሰራለን ብለን እንጠብቃለን" ብለዋል።

ከጥቅምት 25 እሰከ ሕዳር 3/2009 ዓም ድረስ በአዳማ፣ ሀረር፣ ሻሸመኔ፣ ነቀምትና ጅማ ከተሞች እየተካሄደ ባለው የጥልቅ ተሃድሶ መድረክ ላይ ከ5 ሺህ 350 በላይ መካከለኛ አመራሮች እየተሳተፉ ናቸው። 

የመድረክ ዋና አላማ በክልሉ የተጀመረውን የመስመር ማጥራት እርምጃ ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋር ያለመ መሆኑም ቀደም ብሎ ተገልጿል -(ኢዜአ) ።