በአማራ ክልል የዳኝነት አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ተዘዋዋሪ ችሎቶችን የማስፋፋት ሥራ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች በተጨማሪ 513 ተዘዋዋሪ ችሎት ጣቢያዎች ተቋቁመው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት የኔነህ ስመኝ ለዋልታ ገልጸዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት 37 ተዘዋዋሪ የችሎት ጣቢያዎችን በተመረጡ አካባቢዎች በማስፋፋት ተዘዋዋሪ ችሎት ጣቢያዎችን 550 ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል ፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን በሰሜን ጎንደር፣ በሰሜን ሸዋና በምዕራብ ጎጃም በሚገኙ የወረዳ ፍርድ ቤቶች ዘጠኝ ንዑስ ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በደብረብርሃን፣ ደሴና ጎንደር ላይ ዓመቱን ሙሉ አገልግሎት የሚሰጡ ሶስት የክላስተር ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም ተደራሽነቱን ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሆነም ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል፡፡
ከጠቅላይ ፍርድ ቤት እስከ ወረዳ ያሉት ፍርድ ቤቶች ተዘዋዋሪ ችሎት ጣቢያዎችን በመጠቀም በሰሩት ሥራ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ነው ፕሬዚዳንቱ ያስገነዘቡት፡፡
አቶ የኔነህ እንዳሉት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሰባት ጣቢያዎች፣ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በ39 ጣቢያዎች፣ ወረዳ ፍርድ ቤቶች ደግሞ በ467 ጣቢያዎች ተዘዋዋሪ ችሎቶችን በመጠቀም ተደራሽ የዳኝነት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
ባለፈው ዓመት ከቀረቡት በርካታ ጉዳዮች በእነዚህ ችሎቶች አማካኝነት ለ54ሺ 87 ጉዳዮች እልባት በመስጠት 242ሺ 492 ባለጉዳዮችን ለማስተናገድ መቻሉን ነው ያስረዱት ፡፡
ባለጉዳዮቹ መደበኛ ፍርድ ቤቶች ወዳሉባቸው አካባቢዎች ቢመላለሱ ለትራንስፖርትና ለተለያዩ ጉዳዮች ሊያወጡ የነበረውን 29 ሚሊዮን ብር ማስቀረት መቻሉን ገልጸዋል ፡፡
ተዛዋዋሪ ችሎቶቹ ባለጉዳዮችን ከወጭ ከመታደግ በተጨማሪ ጊዜን ለመቆጠብ፤ ረጅምና አድካሚ የእግርና የትራንስፖርት ጉዞ ለማስቀረት የጎላ ሚና አብራርተዋል ፡፡
ተገልጋዮች የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን ቅጅ ለመቀበል ለማመልከቻ ማፃፊያ ለግለሰቦች የሚያወጡትን እስከ 100 ብር የሚደርስ ወጭን ለማስቀረት የሚረዳ ፎርም እንዲዘጋጅ መደረጉም አመልክቷል፡፡