በአማራ ክልል አምባጊወርጊስ ከተማ ደሴ ስጦታው የተባለ ወጣት በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተከሶ ድርጊቱን መፈፀሙ በማስረጃ በመረጋገጡ በ6 ዓመት ከ6 ወር በእስራት ተቀጣ፡፡
ተከሳሽ የግል ተበዳይን በጩቤ በማስፈራራት በፈፀመው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል መቀጣቱን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለዋልታ ገልጿል፡፡
ተከሳሹ ጥቅምት ዐ5 ቀን 2ዐዐ9 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 8፡ዐዐ ሰዓት አምባጊወርጊስ ከተማ ልዩ ስሙ አንጅባ በተባለ ቦታ የግል ተበዳይን በጩቤ በማስፈራራት አስገድዶ በመድፈር ክብረንፅሕናዋን መግሰሱ በክሱ ተመልክቷል፡፡
የወገራ ወረዳ ፍትህ ጽህፈት ቤት የወንጀል የሥራ ሂደት ዐቃቢ ሕግ ከላይ በተጠቀሰው ቀን ለወገራ ወረዳ ፍርድ ቤት አንደኛ የወንጀል ችሎት ባቀረበው ክስ ተከሣሹ የወንጀል ሕግ ቁጥር 62ዐ/11ን በመተላለፍ ወንጀል መፈፀሙን በመጠቆም ክስ መስርቷል፡፡
ተከሣሽ ችሎት ላይ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል የወንጀል ድርጊቱን መፈፀሙን አምኖ ከተበዳይ ጋር የፈፀመው የግብረስጋ ግንኙነት በፈቃዷ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ተከሣሽ በከፊል ክዶ የቀረበ በመሆኑ እንደካደ በመያዝ ዐቃቢ ሕግ ማስረጃ አስቀምጧል፡፡
ከሣሽ ተበዳይ ነኝ በማለት ባቀረበችው ክስ በተጠቀሰው ቦታ፣ቀንና ሠዓት ከልብስ ገበያ ላይ ተከሣሽ በጩቤ በማስፈራራት አብራው እንድትሄድ እንዳስገደዳት ትናገራለች፡፡
ከዛም ባዶ ቤት በማስገባት በጩቤ እያስፈራራ የግብረስጋ ግንኙነት ፈፅሞባት ጠዋት ሊነጋ ሲል በሩን በውጭ ዘግቶባት ሄዶ በማግስቱ ፖሊስ በሩን እንደከፈተላት መስክራለች፡፡ በሩን የከፈተላት ፖሊስም ተዘግታ እንዳገኛት ቃሉን ሰጥቷል፡፡
ክብረንፅሕናዋ መወሰዱም በወገራ ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተረጋግጧል፡፡ ጥቅምት 16ቀን 2ዐዐ9 ዓ.ም የዋለው ችሎትም ተከሳሽ ቀደም ሲል የወንጀል ሪከርድ ያልተመዘገበበት መሆኑ እንደ አንድ ቅጣት ማቅለያ ተይዞለት እጅ ከተያዘበት ዕለት በሚታሰብ በስድስት ዓመት ከስድስት ወር እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡