በድርጅቱ ውስጥ እየገነገኑ የመጡት ጸረ-ዲሞክራሲ አሰራሮችና አብዮታዊ ያልሆኑ ስነ ምግባሮችን በመጠየፍ ለመታገል ቆርጠው መነሳታቸውን የህወሓት መካከለኛና ጀማሪ አመራሮች አስታወቁ ፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኙ የድርጅቱ አመራሮች ከህዳር 9 እስከ 14/2009 ዓመተ ምህረት ድረስ ባካሄዱት ጥልቅ ተሃድሶ ባለፉት 15 ዓመታት በሰላም ፣በልማት፣በዲሞክራሲና በመልካም አስተዳደር የተገኙ ድሎችና ጉድለቶች ዙሪያ በሰፊው በመገምገም ውሳኔ አስተላልፈዋል ፡፡
አመራሮቹ የውስጠ ድርጅት ባለመጠናከሩ ምክንያት እየገነገኑ የመጡ ጸረ ዲሞክራሲያዊ አሰራሮችንና አብዮታዊ ያልሆኑ ስነ ምግባሮችን በመጠየፍ የሚታዩትን የጠባብነትና አከባቢነትን ለመመከት እንደሚረባረቡ አረጋግጧል ፡፡
የህዝቡ ጥቅምና መብት ማስክበር የሚቻለው የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ ነው ያለው የአቋም መግለጫው፤ የሁሉም ጉድለቶች ምንጭ የሆነው የያዝከውን ስልጣን ለህዝብ አገልግሎት ያለማዋል ችግር ከስር መሰረቱ ለመንቀል እንደሚረባረቡ አስታውቋል ፡፡
ከህዝባዊ ውግንናቸው ማነስ ተያይዞ የተፈጠረው የመልካም አስተዳደር ችግር ለማረም ፖለቲካዊ ብቃትና ውሳኔ የመስጠት ባህላቸውን በማሳደግ እምርታ ለማስመዝገብ እንደሚጥሩ ገልጸዋል ፡፡
አማራሮቹ በመስመሩ እያጋጠሙ ያሉት አደጋዎች ለመመከት የህዝብ እርካታ ለማረጋገጥ በድርጅቱ ውስጥ የተጋጋለ ትግል መፍጠር ግዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል ፡፡
ለዚሁም የድርጅቱ ህዝባዊነት ወደ ነበረበት በመመለስ ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ህዝቡን ለመካስ ቃል ገብተዋል ፡፡
በወጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መሰረት የተመዘገቡ አንጸባራቂ ድሎች በማጣጣም በድርጅቱ ውስጥ የተፈጠሩ ፈተናዎች በማስወገድ ድርጅቱ ለመድረካዊ ተልዕኮው ለማብቃት እንደሚረባረቡ አስታውቀዋል ፡፡
ከሁሉም በፊት አባሉ ራሱን በማደስ እና በተሃድሶ መስመር ጥላ ስር በመሆን በጊዜ የለም አስተሳሰብ ለመታገል ወስነዋል ፡፡
ዲሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለማጥለቅ አስፈላጊ የሆኑ ምክርቤቶች ፣ህዝባዊ ድርጅቶችና ሌሎች ተቋሞች ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ በሚደረገው የማጠናከር ስራ ልዩ ሚና ለመፈጸም ቃል ገብተዋል ፡፡
ልመታዊና ዲሞክራሲያዊ መስመሩን በአደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር መሆናቸውን በመረዳት የያዙትን ተልዕኮ ለማሳካት እንደሚታገሉ ገልጸዋል ፡፡
የወጣቶችና ሴቶች ተሳታፊነታቸውና ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት የአመራር ሚናቸውን በአግባቡ እንደሚፈጽሙ አረጋግጧል ፡፡
በህዝቡ የተፈጠረው ያለመርካት እንደ መልካም ዕድል በመውሰድ ህዝቡንና መሪ ድርጅቱን ለመለያየት ሌት ተቀን የሚጥሩ የውስጥና የውጭ ጸረ ህዝብና ጸረ ሰላም ኃይሎች በጽናት እንደሚታገሏቸው አስታውቀዋል ፡፡
ከኢህአዴግና እህት ዲሞክራሲያዊ ደርጅቶች ጋር በመሆን የትምክህትና የጠባብ ሃይሎች ያሚያደርጉት ጸረ ህገ መንግስትና ጸረ ህዝብ እንቅስቃሴ በጽናት የሚታገሉ መሆናቸውን አስገንዝበዋል ፡፡