ኢትዮጵያ በማራካሹ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ተሳትፎዋ የጎላ ነበር

ኢትዮጵያ በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በማራካሹ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ  የጎላ  ሚና መጫወቷን የአካባቢ ደንና  የአየር ንብረት ለውጥ  ሚኒስቴር አስታወቀ ።                        

በሞሮኮ ማራካሽ  የተካሄደው  ጉባኤ  ዓምና  ከተካሄደው የፓሪሱ  የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በመቀጠል  የተከናወነ ሲሆን  አገራት   የፓሪሱን  ስምምነት  እንዲፈርሙና ተግባራዊ እንዲያደርጉ   ግፊት   ለማሳደር  ተብሎ   የተዘጋጀ ነው  ።    

የፓሪሱ  ስምምነት  በዓለም  ላይ የአየር  ንብረትን ለውጥ  ተጽዕኖን  ለመከላከል የሚያስችል  ፈር ቀዳጅ  ስምምነት  እንደሆነ የሚነገርለት ሲሆን   170  የሚደርሱ አገራት በማራካሽ  ስምምነቱ  ላይ ፊርማቸውን   አኑረዋል ።

 የአካባቢ  ደንና የአየር ንብረት ለውጥ  ሚኒስትር  ዶክተር ገመዶ ዳሌ በትናንትናው  ዕለት  በሠጡት መግለጫ  ኢትዮጵያ  በደን ልማትና  በስነምህዳር ጥበቃ   የተለያዩ  ሥራዎችን ማከናወኗ  ለሌሎች  አገራት  እንደ ምሳሌ የሚወሰድ ነው ብለዋል ።   

የአገሪቷ  የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲም ከዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ተግባራትና እርምጃዎች  ጋር  ተጣጥሞ የሚሄድ መሆኑን የጠቆሙት   ዶክተር ገመዶ  ኢትዮጵያ  የታዳሽ የኃይል ምንጮችን  በማስፋፋት  በዓለም  የፀረ – የአየር ንብረት ለውጥ ተከራካሪ መሆን  ችላለች ብለዋል ።

ኢትዮጵያ  በዓለም   የአየር  ንብረት ለውጥ  በከፍተኛ ደረጃ  ተጋላጭ   የሆኑ  47 አገራትን  በማሰባሰብ  በአየር ንብረት ላይ ከፍተኛ  ብክለት   የሚያደርሱ አዳጊ  አገራት   ለታዳጊ  አገራት   ካሳ  እንዲከፍሉ  በመከራከር ላይ መሆኗን  ዶክተር ገመዶ ተናግረዋል ።  

ሁሉም  የፓሪሱ  ስምምነት  ፈራሚዎች  የአየር ንብረት ለውጥ  እርምጃዎችን  ተግባራዊ ለማድረግ  የሚያስችሉ  መምሪያዎችን  እኤአ በ2017 በማውጣት   እኤአ በ2018  መመሪያዎችን የማውጣት  ሥራን  ሙሉ ለሙሉ በማጠናቀቅ  በእኤአ በ 2020  ስምምነቱን ተግባራዊ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ።