በአገሪቱ የሚገኙ ወጣቶችን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ አዲስ የወጣቶች የልማትና ዕድገት ፓኬጅ ማዘጋጀቱን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ ።
ሚንስትሩ አቶ ርስቱ ይርዳው በዛሬው ዕለት በሠጡት መግለጫ እንደገለጹት ከባለፉት ዓመታት ጠንካራ ተሞክሮዎችና ድክመቶች ልምድ በመውሰድ በአገሪቱ በገጠር፣ ከተማ፣ በአርብቶ አደር ነዋሪዎችና ልዩ ድጋፍ የሚሹ ወጣቶች ያካተተ እንዲሁም በተሻለ ደረጃ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የወጣቶች የልማትና ዕድገት ፓኬጅ ተዘጋጅቷል ።
አዲስ ፓኬጅ ማዘጋጀት ያስፈለገው ወጣቱ በአገሩ ልማትና ፖለቲካ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ለማስቻል መሆኑን የጠቆሙት አቶ ርስቱ ይበልጥ የወጣቱ ህብረተሰብ ክፍል ለሚያቀርበው የተጠቃሚነትና የተሳትፎ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ የሚሠጥ ነው ብለዋል ።
አዲሱ ፓኬጅ ፀድቆ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት የተለያዩ ባለድርሻዎች በተለይም የወጣት ማህበራት ፣ አደረጃጃቶች እንዲወያዩበት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ ርስቱ ፓኬጁ ተግባራዊ ሲደረግ የወጣቱ ህብረተሰብ በአገሩ ጉዳይ ላይ የመወሰን አቅሙን ከፍ ለማድረግ እንደሚያግዝ አመልክተዋል ።
በቅርቡ በመንግሥት የተመደበው ተጨማሪ 10 ቢሊዮን ብር የወጣቶች ተንቀሳቃቀሽ ፈንድ የአዲሱ ፓኬጅ አካል መሆኑን የሚናገሩት አቶ ርስቱ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ወጣቶች አዋጪ የሥራ ፕሮጀክቶችን ለተለያዩ አካላት በማቅረብ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል እየተመቻቸ እንደሚገኝ አስረድተዋል ።
ተንቀሳቃሽ ፈንዱን ሥራ ላይ ለማዋል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የህግ ማዕቀፍና መመሪያ እያተዘጋጀ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ርስቱ በቅርቡ ፈንዱ በምን ሁኔታ ጥቅም ላይ እንደሚወል የሚገልጽ ብሔራዊ የማስተዋወቅ ፕሮግራም እንደሚኖር ገልጸዋል ።