የግንቦት ሰባት  88 አባላት ሙትና ሙርኮኛ መሆናቸውን ሚኒስቴሩ አስታወቀ ፡፡

ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ሰርጎ ለመግባት የሞከረው የግንቦት ሰባት  88 የጥፋት ኃይል አባላት ሙትና ሙርኮኛ መሆቸውን የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በብርሃኑ ነጋ የሚመራው ግንቦት 7  ሰሞኑን በምዕራብ ትግራይ ዞን ሰርጎ ለመግባት የሞከረው  113 የታጠቀ የሰው ሀይል 15ቱ ሲገደሉ 73ቱ ሊማረኩ መቻላቸውን ነው የገለጸው ።

በሀገሪቱ ተፈጥሮ የነበረውን ሁከትና ብጥብጥ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የጥፋት ሃይል በዞኑ ህዝብና ሚሊሻ በቁጥጥር ስር መዋሉን ሚኒስቴሩ አመልክቷል ።

መሪዎቹን ጨምሮ ሌሎችም የመሪነት ሚና የነበራቸው የጥፋት ሀይሎች በዞኑ ህዝብና ሚሊሻ   ተከታትሎ በማደን በወሰደው እርምጃ ሊደመሰሱና ሊማረኩ መቻላቸውንም ነው ያስረዳው ።

በሁለት ዙር የገቡት እነዚህ የጥፋት ሀይሎች የመጀመሪያው ዙር በሻለቃ መስፍን ጥጋቡ የሚመራ ሲሆን ፤ ሁለተኛው ደግሞ በደስታው ተገኝ ይመራ እንደነበር አብራርቷል።

 

ከጦር መሳሪያዎች እና ሌሎች ቁሳቁሶች ባሻገር በርካታ የኢትዮጵያ ብርና የአሜሪካ ዶላር በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቋል ።

የምዕራብ ትግራይ ዞን ህዝብና ሚሊሻ የተበታተኑትን ጥቂት የጥፋት ሀይሎች እየተከታተለ ይገኛል ያለው የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር፥ ሻዕቢያ፣ አርበኞች ግንቦት 7ም ሆነ ሌሎች የጥፋት ሀይሎች በተሳሳተ ስሌት የአገራችንን ሰላም ማወክም ሆነ ልማታችንን ማደናቀፍ ፈፅሞ እንደማይሳካላቸው ያስተማረ እርምጃ መወሰዱን ነው ያስገነዘበው ።

ሚኒስቴሩ ሻዕቢያና ደጋፊዎቹ እንዲሁም የሀገራችን ሰላምና ልማት የማይዋጥላቸው የጥፋት ሀይሎች ከንቱ ሴራ ፈፅሞ አይሳካም  ሲል ነው ያስታወቀው  -(ኤፍ.ቢ.ሲ)።

 

ከጥፋት ሀይሎቹ የተማረኩ የጦር መሳሪያዎች፣ ተተኳሾችና ቁሳቁሶች አይነት እና ብዛትም ከዚህ በታች ተዘርዝሯል።

1. ክላሽንኮቭ ጠመንጃ – 73 

2. የእጅ ቦምብ – 62

3. ከባድ መትረየስ – 2

4. አር ፒ ጂ – 1

5. ስናይፐር – 2 

6. ሽጉጥ – 5

7. ቱሪያ ሳተላይት መገናኛ – 2

8. የጦር ሜዳ መነፀር – 5

9. ዲጂታል ካሜራ – 1

10. መረጃ የያዙ ፍላሾች – 8

11. ሶላር – 1 

12. ተንቀሳቃሽ ስልክ – 5