የአማራ ክልል ምክር ቤት የስምንት ዳኞችን ሹመት አጸደቀ

የአማራ ክልል ምክር ቤት የስምንት ዳኞችን ሹመት ማፅደቁን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

ዳኞቹ የተሾሙት ለብሔረሰብ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶችና ለወረዳ ፍርድ ቤቶች መሆናቸውን የፍርድ ቤቱ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ አለምሸት ምህረቴ ለዋልታ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ለአዊ ማህበረሰብ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሶስት ዳኞች እንደዚሁም ለዋግኽምራ ብሔረሰብ ዞን ደግሞ አንድ የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛ ተሹመዋል ነው ያሉት ፡፡

በተመሳሳይም ለኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አንድ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛና ሶስት የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞች መሾማቸውን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

ዳኞቹ በብሔረሰብ ዞን ምክር ቤቶች ተገምግመውና ተተችተው ለሹመት መመረጣቸውን ነው አቶ አለምሸት ያስረዱት፡፡

የትምህርት ዝግጅታቸው፣የሥራ ልምዳቸው፣ሥነ ምግባራቸውና ሌሎች መስፈርቶችን አሟልተው በመገኘታቸው መሾማቸውን አብራርተዋል፡፡

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዓሊ መሀመድ የዳኞቹ ሹመት የተቀላጠፈና እውነተኛ ፍርድ ለመስጠት ዋናው ግብዓት መሆኑን ነው የገለጹት ፡፡

የቀጠሮ ፖሊሲን መሰረት ያደረገና የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት የሚያስችል ዳኝነት ለመስጠት የዞኑን የዳኞች ቁጥር ከ17 ወደ 21 መጨመሩ ጉልህ ሚና እንዳለው ነው ያስገነዘቡት ፡፡

የተሾሙት ዳኞች ዞኑ ተደራሽ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት የጀመረውን ጥረት እንደሚያጠናክር ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል ፡፡

የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና አምስት የወረዳ ፍርድ ቤቶች  እንዳሉት ከዞኑ የተገኙት መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ በወረዳ ፍርድ ቤቶች ተዘዋዋሪ ችሎቶች ተግባራዊ መሆናቸውን አስታውቀዋል ፡፡

የፕላዝማ ችሎትን ለማቋቋምም ዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡