በአገሪቱ የተጀመረው የታሃድሶ ንቅናቄ ሂደት ውጤታማ የሚሆነው መላው የአገሪቱ ህዝቦች የማያቋርጥና የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ ።
ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም በዛሬው ዕለት በሐረር ከተማ 11ኛው የብሔር ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት በአገሪቱ እየተካሄደ ያለው ጥልቅ ታሃድሶ ውጤት እንዲበቃ ሁሉም ህብረተሰብ ያሳተፈ ንቅናቄ ሲደረገ ነው ።
በመሪው ፓርቲ ኢህአዴግና በአጋር ድርጅቶቹ የተጀመረው ጥልቅ የታሃድሶ ንቅናቄ መላው የህብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተና የማደስ አቅምም እንዳለውና በቅርቡ የገጠሙትን የአስተሳሰብ ዝንባሌዎችና ጉድለቶችን ለመሙላት የሚያስችል መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትሩ ገልጸዋል ።
በኢትዮጵያ ህገ መንግሥት እንደተቀመጠው ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ለማበልጸግ ላለፉት ዓመታት አጅግ አበረታች ሥራዎች እንደተካሄዱ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን የጋራ ጥቅሞችን ለማስከበር ባለፉት 22 ዓመታት በአንድነትና በተደጋጋፊነት ለማሳደግ የተገባውን ቃል ኪዳን ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል ።
የህገ መንግሥቱ ሰነድ ከጅማሬው አንስቶ የህዝቦችን መልካም እሴቶችን ፣ የጋራ ጥቅሞችንና አመልካከትን በማጎልበት አንድ ጠንካራ የኢትዮጵያን ማህበረሰብ ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑ ታምኖበት ነው ብለዋል ።
ዘንድሮ የ11ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን ስናከብር ህገ መንግሥቱን ስናጸድቅ የገባነውን ቃል ኪዳን በማጽናትና በተግባርም ለማስመስከር በማሰብ መሆኑን ው ያስገነዘቡት ።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በመተሳሰብና በመመካከር እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ አገራዊ አንድነትን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ አስረድተዋል ።
የህዝብና የመንግሥት ሃብትን አላግባብ ለግል ጥቅም የመዋል ዝንባሌንና ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከልም በተለያዩ ደረጃዎች የሚካሄዱ ጥልቅ ታሃድሶዎችና እርምጃዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅላይ ሚንስትሩ አያይዘው አስታውቀዋል ።
በመጨረሻም ጠቅላይ ሚንስትሩ 11ኛው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በድምቀት እንዲከበር ላደረገው የሐረሪ ብሔራዊ ክልል መንግሥትና ህዝብ ታላቅ ምስጋና አቅርበዋል ።
የ11ኛው የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል “ ህገ መንግስታችን፣ ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችንና ለህዳሴያችን" በሚል መሪ ቃል የተከበረ ሲሆን 12ኛው የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል አዘጋጅነት ለአፋር ክልል ተሠጥቷል ።