የሱዳንና ጅቡቲ መሪዎች በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ላይ መልካም ምኞታቸውን ገለጹ

የሱዳንና ጅቡቲ መሪዎች በሐረር ከተማ እየተከበረ  በሚገኘው  11ኛው የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ላይ ተገኝተው  ለመላው   የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች  የእንኳን አደረሳቹህ መልካም  ምኞታቸውን ገልጸዋል ።

የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር በሐረር ስታዲየም ተገኝተው  ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ  ህገ መንግሥቱን ባፀደቀበት ዕለት ለሚያከብረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል እንኳን አደረሰው ብለዋል።

የሐረር ከተማ ለዘመናት ያቆየቺውን የፍቅርና የመቻቻል የባህል እሴት ጠብቃ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን በዓል ማዘጋጀቷ ትልቅ ትርጉም የሚሠጠው መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚደንት አልበሽር  ለሌሎችም እንደ ምሳሌነት የምትታይ  መሆኗን ነው የገለጹት

የኢትዮጵያና ሱዳን ግንኙነት በፖለቲካውና በኢኮኖሚው ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም  ፕሬዚደንት  አልበሽር  ተናግረዋል ።

የሁለቱን አህትማማቾች አገራት ግንኙነትን ይበልጥ  ለማጠናከር በተለያዩ  መስኮች  የሚያደርጉትን  ትብብር ይበልጥ  ለማጎልበት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል ።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ  ሰላምና ፀጥታ እንዲሰፍን  የምታደርገውን ጥረት ሱዳን የምትደግፍ መሆኑን  የገለጹት ፕሬዚዳንት አልበሽር  ሱዳን በክፍለ አህጉሩ የሰላም ጉዳይ   ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ አቋም እንዳላት አረጋግጠዋል ።

የጅቡቲው ፕሬዚደንት እስማኤል ኡመር ገሌ በበኩላቸው  መላው  የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለ 11ኛው  ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችናሕዝቦች በዓል አደረሳቹህ በማለት  በዓሉ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ግንኙነት ይበልጥ የሚያጎለብት መሆኑ  አስገንዝበዋል ።

ለኢትዮጵያ  ህዝብ ሰላም ፣ ህዳሴንና ብልጽግናን  የተመኙት   ፕሬዚደንት  እስማኤል ኡመር ገሌ    የጅቡቲና የኢትዮጵያ  ግንኙነት   በጋራ ተጠቃሚነት ላይ  የተመሠረተ መሆኑን አንስተዋል ።