የብሔሮች፣ብሔሰቦችና ህዝቦች በዓል በሰላም መጠናቀቁን ፖሊስ አስታወቀ

በሐረር ከተማ የተከበረው 11ኛው የብሔሮች፣ብሔሮችና ህዝቦች ቀን በዓል በሰላም መጠናቀቁን የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ ፡፡

በዓሉ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ህብረተሰቡን በማስተባበር የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች በፈጸሙት ስራ ምንም ዓይነት የተከሰተ ወንጀል ሳያጋጥም መጠናቀቁን  የኮሚሽኑ ህዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ጣሰው ቻለው ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ገልጸዋል ፡፡

ይህም የሆነው ከበዓሉ ዋዜማ አንስቶ ከየክልሉ የመጡ እንግዶች ማረፊያ ቤታቸው እሰከሚገቡ ድረስ ፖሊስ በገጠርና በከተማ ተሰማርቶ ጥንቃቄ የተሞላበት ጥበቃ  በማድረጋቸው መሆኑን አስረድተዋል ፡፡

ኮሚሽኑ ከሁለት ወር በፊት የጸጥታ ሰራዊቱን በስነ ልቦና  እና በአካል ብቃት በማዘጋጀት ስራውን እንዴት ማከናወን እንዳለበት  ሰፊ ዝግጅት መደረጉን ነው የገለጹት ፡፡

ለዚህም ከአጎራባች ፖሊሶች ጋር፣ ከሀገር መከላከያና ከፌደራሎች ፖሊስ ጋር ጥምረት በመፍጠር  ጠንካራ የጸጥታ ስራ መከናወኑን አስገንዝበዋል ፡፡

እንደዚሁም ከኮማንድ ፖስት ጋር ዕቅድ በማውጣት እስከ ንኡስ ኮማንድ ፖስት ድረስ ስራውን የሰራንበት ሁኔታ ነበር ነው ያሉት ፡፡

በተለይም በክልሉ ኮሚኒቲ ፖሊሲንግ በኩል ከፍተኛ ስራ ሰርተናል ያሉት ኮማንደር ጣሰው ፤ ይህም ወጣት ማህበራትን  በማደራጀት እስከ ታች መንደር ድረስ ጥበቃ ስራው እንዲጠናከር ማድረጋቸውን ነው ያብራሩት  ፡፡

በዚሁም ህብረተሰቡ መረጃ በመስጠት፣ ዘብ  በመውጣት፣ ከጸጥታ ኃይሎች ጋ በፍተሻ ስራ ጭምር  በመሰማራት ቀንና ሌሊት በመጠበቅ ረገድ  ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበረከታቸውን አስታውቀዋል ፡፡

ይህም ህብረተሰቡ በከተማ አስጊ የሆኑ ጠጉረ ልውጥ ሰዎችን ሲመለከት መረጃ  በመስጠት ራሱ ይዞ ለፖሊስ በማቅረብ ጭምር  እጅግ አርኪ ስራ ማከናወኑን አብራርተዋል  ፡፡

ለበዓሉ የመጡ ከ3ሺ በላይ የብሔሮች ፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተወካዮች በሰላምና መረጋጋት ታጅበው  ወደየመጡበት መሸኘታቸውን ኃላፊው አስታውቀዋል ፡፡

በዓሉ በሰላም እንደጠናቀቅ ላደረጉት የጸጥታ ኃይሎችና ህብረተሰቡ   ምስጋናቸውን ያቀረቡት ኮማንደር ጣሰው ፤  በክልሉ ቀደም ብሎ  የተከፈተው ኤግዚብሽንና ባዛር ታህሳስ 2/2009 ዓመተ ምህረት  እስኪጠናቀቅ ድረስም ጥበቃው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል ፡፡