ታላቁ የህዳሴ ግድብ የህዝቦች የዲሞክራሲያዊ አንድነት መገለጫ ነው

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የዲሞክራሲያዊ አንድነት መገለጫ መሆኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

ኢትዮጵያውያን ያለምንም ብድርና እርዳታ በይቻላል መንፈስ ለዘመናት በአይደፈሬነት የቆየውን የአባይን ወንዝ በፍትሃዊነት ለመጠቀም የበኩላቸውን ያልተቋረጠ ድጋፍ በማድረግ አንድነታቸውን በተግባር ማረጋገጣቸውን ፅህፈት ቤቱ ለዋልታ በላቀው መግለጫ አመልክቷል፡፡

በራስ አቅም እየተገነባ ለሚገኘው ግድብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የአቅሙን ያህል ድጋፍ በማድረግ ግንባታው በተያዘለት ዕቅድ መዘረት እየተከናወነ እንደሚገኝ ፅህፈት ቤቱ አስረድቷል፡፡ በዚህም በድህነት ላይ ድልን ለመቀዳጀት ህዝቡ ቆርጦ መነሳቱን ገልጿል፡፡

በተለይም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አገሪቱ የተለያዩ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ቢጋጥሟትም ህዝቡ ችግሮቹን በመቋቋምና በመከላከል ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ አለሟቋረጡ አንስቷል፡፡

በመግለጫው እንደተመለከተው የህዳሴው ግድብ ዋንጫ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በመዘዋወር ከፍተኛ ገቢ እያሰባሰበ ነው፡፡

እስከ አሁንም በአምስት ክልሎች የተዘዋወረ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል በሁሉም ዞኖችና ከተሞች ተዘዋውሮ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገባቱ ለአብነት ጠቅሷል፡፡

በክልሎች የታየው ርብርብ የዲሞክራሲያዊ አንድነቱ ተጨባጭ መገለጫ መሆኑን መግለጫው አስታውሶ ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ በመያያዝ ግዙፍ ልማቶችን ዕውን ለማድረግ ትግላቸውን ማጠናከራቸውን አስታውቋል፡፡

ልማታዊ ርብርቡ ህዝቦች በድህትና ኋላቀርነት ላይ አንፀባራቂ ድሎችን በመጎናፀፍ የምግብ ዋስትናን እንዲያረጋግጡ ማስቻሉን ገልጿል ፡፡

ህገ መንግስታዊ የፌዴራል ሥርዓቱ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለአገራቸው ልማና ዕድገት በንቃት የሚሳተፉበትን ዕድል መፍጠሩንም እንዲሁ ፡፡

11ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ትናንት በሐረር ከተማ ‹‹ህገ መንግስታችን ለዲሞክራሲያችንና ለአንድነታችን›› በሚል መሪ ቃል በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፡፡