በአገሪቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠሩ ሁከቶች በመሳተፋቸው ምክንያት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ከተደረጉት 11ሺ 600 የሚሆኑት ሰዎች መካከል 9ሺ 800 የሚሆኑት በመጪው ረቡዕ ዕለት እንደሚለቀቁ ተገለጸ ።
የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬቴሪያትና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በዛሬው ዕለት በሠጡት መግለጫ እንደገለጹት በአንዳንድ አካባቢዎች ከተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ ጋር ተያይዞ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ከተደረጉት 11ሺ 600 መካከል 9ሺ 800 የሚሆኑት በአምስት ማዕከላት የተሃድሶ ሥልጠና ሲከታተሉ ቆይተዋል ።
በመጀመሪያ ዙር በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ውስጥ ወደ 2 ሺ የሚጠጉት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑና 9ሺ 800 የሚሆኑት ደግሞ በተሃድሶ ታርመው እንዲወጡ ኮማንድ ፖስቱ መወሰኑን የጠቆሙት አቶ ሲራጅ በተሃድሶው የታራሚ ሥልጠናቸውን ያጠናቀቁት በመጪው ረቡዕ ተመርቀው ወደ ህብረተሰብ ይቀላቀላሉ ብለዋል።
የተሃድሶ ሥልጠና ያገኙት ሰዎች በቀጣይ በአገሪቱ የሰላምና የልማት ሃይል ለመሆን እንደሚሠሩ በቂ መግባባት የተፈጠረላቸው መሆኑንና ባገኙት ሥልጠና ለአገራቸው ገንቢ ሚናን ለመጫወት ግንዛቤ እንዳገኙ አቶ ሲራጅ አብራርተዋል ።
እንደ አቶ ሲራጅ ገለጻ ኮማንድ ፖስቱ በመጀመሪያው ዙር በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ተሳትፈው በቁጥጥር ሥር ያልዋሉና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጣስ ተጨማሪ ሁከትና ብጥብጥን ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 12ሺ 500 ተጠርጣሪ ግለሰቦች በ2ኛው ዙር በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ አድርጓል ።
ህብረተሰቡ በሁከት የተሳተፉ ግለሰቦችን በመጠቆም በኩል የላቀ ሚና መጫወቱን የገለጹት አቶ ሲራጅ በሁለተኛ ዙር የተያዙት ተጠርጣሪዎችም በሁከቱ ላይ የነበራቸው ሚናን በመለየት በህግ እንዲጠየቁና የተሃድሶ ሥልጠና እንዲያገኙ ጥረት ይደረጋል ብለዋል ።
ሁከት በተፈጠሩባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የቀበሌ አስተዳደሮች፣ የገበሬዎች ማሠልጠኛ ጣቢያዎችና የጤና ኬላዎች መውደማቸውን የተናገሩት አቶ ሲራጅ በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡ የወደሙትን ተቋማት መልሶ በመገንባትና የቀበሌ መዋቅሮች የማደራጀት ሥራዎች በማካሄድ ተቋርጦ የነበሩት የማህበራዊ አልግሎቶችን ማስጀመር ተችሏል ።
ከተከሰቱት ሁከቶች ጋር በተያያዘ በአንዳንድ አካባቢዎች የመንግሥትና የህዝብ ንብረቶች የሆኑ ግምጃ ቤቶች፣ ንብረቶችና የጦር መሣሪያዎች መዘረፋቸውን የጠቆሙት አቶ ሲራጅ ህብረተሰቡን ባደረገው የላቀ ተሳትፎ የተወሰዱት ንብረቶችና የጦር መሣሪያዎች መመሰላቸውን አብራርተዋል ።
ከፌደራል እስከ ክልል ድረስ የተደራጀው የኮማንድ ፖስቱ መዋቅሩ አዳዲስ ኬላዎችን በማደራጀት ሽብርን ለማባባስ የሚውሉና በህገ ወጥ መልኩ ሲዘዋወሩ የተገኙ የጦር መሣሪያዎች ፣ የሞተር ሳይክሎችንና የመገናኛ መሣሪያዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አቶ ሲራጅ አመልክተዋል ።
በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ብጥብጥ ወደማያቋርጥ ደረጃ እንዲደርስ ለማድረግ የሚጥሩት የሻቢያና መንግሥትና ግንቦት ሰባት የተደራጁ የሽብር ሃይሎችን በመላክ አገሪቱን ለማተራመስ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አቶ ሲራጅ አያይዘው ገልጸዋል ።
ሻቢያና ግንቦት ሰባት በመጀመሪያ ዙር 30 አባላት ያሉት ቡድንና በሁለተኛው ዙር 87 አባላት ያለውን የሽብር ታጣቂ ቡድኖችን የተላኩ መሆኑን የገለጹት አቶ ሲራጅ በአጠቃላይ 87 የሚሆኑት በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና 14 የሚሆኑት ደግሞ መደምሰሳቸውን አስረድተዋል ።
ኮማንድ ፖስቱ ከተለያዩ የአገር ውስጥ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በፓርቲዎቹ ጠያቂነት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አተገባባር ዙሪያ 58 የሚደርሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በማሳተፍ በአዋጁ ዙሪያ አስፈላጊው ማብራሪያ ተሠጥቷል ።
በተጨማሪም የአስኳቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጻምን ለመከታተል የተቋቋመው የመርማሪ ቦርድ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦችን አያያዝ ላይ በተመለከተ ባቀረበው ሪፖርት መሠረት ኮማንድ ፖስቱ አስፈላጊውን ማስተካካያ ማድረጉን አቶ ሲራጅ በመግለጫቸው ጠቁመዋል ።
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ የሚከናወኑ ሥራዎች ያልተጠናቀቀበት ሁኔታ በመኖሩና የቀሩትን ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ኮማንድ ፖስቱ የያዘውን ሥራ አጠናከሮ እንደሚቀጥል ሚንስትሩ መግለጻቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።