ወንድሞችና እህቷን የገደለችው በ25 ዓመት ፅኑ እሥራት ተቀጣች

በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን የታች ጋይንት ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ጥጋብ መኳንንት ሁለት ወንድሞቿንና እህቷን በመግደሏ በ25 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጥታለች፡፡

ተከሣሽ ወይዘሮ ጥጋብ ሰውን ለመግደል በማሰብ በተለያዩ ጊዜያት በእንግድነት ወደ ቤቷ የመጡትን ወንድሞችና እህቶቿን በመጥረቢያ በመምታት መግደሏ በምስክሮችና በማስረጃ ተረጋግጦ ውሳኔው እንደተላለፈባት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለዋልታ አስታውቋል፡፡

ተከሳሿ ግንቦት 4 ቀን 2ዐዐ8 ዓ.ም በእንግድነት ወደ መኖሪያ ቤቷ የመጣችውን እህቷን ወይዘሮ ዳሣሽ መኳንንትን በግምት ከሌሊቱ 7፡ዐዐ ሰዓት በተኛችበት እራሷን በመጥረቢያ ደጋግማ በመምታት ገድላታለች፡፡

በተመሣሣይም ተከሳሿ ሰውን ለመግደል በማሰብ ቀኑ በውል ባልታወቀበ ት በህዳር ወር 2ዐዐ5 ዓ.ም በእንግድነት ወደ መኖሪያ ቤቷ የሄደውን ወንድሟን አልማው መኳንንትን በግምት ከሌሊቱ 7፡ዐዐ ሰዓት በተኛበት እራሱን በመጥረቢያ ደጋግማ በመምታት መግደሏ ተረጋግጧል ብሏል ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ግንቦት 19 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም በእንግድነት ወደ ቤቷ የሄደውን ወንድምዋን ሟች አባቡ መኳንንትን በግምት ከሌሊቱ 6፡ዐዐ ሰዓት በተኛበት አፍንጫው አካባቢ በመጥረቢያ ደጋግማ በመምታት መግደሏን ገልጿል ፡፡

ተከሳሿ ወንድሞችና እህቷን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ከገደለቻቸው በኋላ ከመኖሪያ ቤቷ ጓሮ በመቅበር ወንጀሉን ለመደበቅ መሞከሯ በክሱ ተመልክቷል፡፡

በዚህም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539/1/ሀ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ለፈፀመችው ወንጀል ተገቢው ቅጣት እንዲተላለፍባት የደቡብ ጎንደር ዞን ፍትህ መምሪያ ዐቃቢ ህግ አመልክቷል፡፡

ተከሳሽ ክሱን እንድትረዳው ከተደረገ በኋላ ፍርድ ቤት ቀርባ በሰጠችው የእምነት ክህደት ቃሏ  "ወንጀሉን አልፈፀምኩም " በማለት ክዳ ተከራክራለች ነው ያለው ፡፡

ዓቃቢ ሕግ ባቀረባቸው የሰው ምስክሮች ወንጀሉን መፈፀሟን በመረጋገጡ እና ተከሣሿ የሰውም ሆነ የሰነድ መከላከያ በማቅረብ ክሱን ማስተባበል አለመቻሏን የደቡብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድቤት አረጋግጧል  ፡፡  

ፍርድ ቤቱ ህዳር 2 ቀን 20ዐ9 ዓመተ ምህረት በዋለው ችሎት ተከሣሿን ያርማል ሌላውን ያስተምራል በማለት በ25 ዓመት ጽኑ አሥራት እንድትቀጣ መወሰኑን አስታውቋል  ፡፡