ሰልጣኞች ወደመደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱ መንግሥት ድጋፍ ያደርጋል-ጠቅላይ ሚኒስትር

በጦላይ የተሃድሶ ማዕከል ትናንት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በባስተላለፉት መልዕክት ሥራ አጥ የሆኑ ወጣቶች በራሳቸው መንገድ ሥራ እንዲፈጥሩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

ሠራተኞችም  ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ የሚደረግ ሲሆን፤ ተማሪዎች ደግሞ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ይደረጋል ብለዋል።

ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የማይነጣጠሉ የአገር ህልውና መሰረት መሆናቸውን ወጣቱ ተገንዝቦ እነዚህን እሴቶች የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ወጣቱ ጥያቄ እንኳ ቢኖረው ሕገ-መንግሥቱ በሚፈቅደው መሰረት የማቅረብና መልስ የማግኘት መብት እንዳለው ገልጸዋል።

ባለፉት ወራት እንደታየው ጥያቄውን በአመጽና ግርግር መጠየቁ ዋጋ እንዳስከፈለ ለማሳያነት በማንሳት።

እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንዳይደገም መንግሥትም የራሱን ስህተት ለማረም ጥልቅ ተሃድሶ እያደረገ መሆኑን ገልጸው ወጣቱም የራሱን ስህተት በማረም ከመንግሥት ጋር ሆኖ ሠላሙን እንዲጠብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው በክልሉ የሰፈነውን ሠላም ለማስቀጠል ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ጋር በቅንጅት ሥራዎች ይሰራሉ ብለዋል።

ከወራት በፊት በተፈጠረው ሁከትና ግርግር ህይወት የጠፋ መሆኑን ገልጸው ለዘመናት የተለፋባቸው የህዝብ ኃብቶችም መውደማቸው አግባብ አለመሆኑን አስገንዝበዋል።

ክልሉ ሊለወጥና ሊለማ የሚችለው የክልሉ ወጣቶች ለሠላም በጋራ ዘብ ሲቆሙ እንደሆነም አስምረውበታል።

አሁን ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ የሚደርስባቸው ነገር እንደማይኖር ገልጸው ተረጋግተው መደበኛ ህይወታቸውን እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

የኦሮሚያ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽነር ፀሃይ በላይ እንደገለጹት ፤ጦላይ ተሃድሶ ማዕከል ከገቡ 5 ሺህ 600 ሰልጣኞች መካከል 4 ሺህ 35 ያህሉ በስድስት ዋና ዋና ጉዳዮች ሥልጠና ወስደው ተመርቀዋል።

"ሰልጣኞቹ በቆይታቸው በፍፁም አይደገምም፣ የቀለም አብዮት፣ የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት የኢትዮጵያ ህዳሴ" በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሥልጠና  መውሰዳቸውን ጠቁመዋል ።

በሁከቱ ተሳታፊዎችም ዘንድ ጥያቄአቸውን በሰላም ከማቅረብ ይልቅ ብጥብጥን መምረጣቸው አግባብ እንዳልነበር ገልጸዋል-( ኢ ዜ አ )፡፡