የሴቶች ስትራቴጂካዊ ልማት ማዕከል በይፋ ሥራ መጀመሩን አስታወቀ

በኢፌዴሪ የበጎ አድራጎት ድርጅት ማህበራት ኤጀንሲ ፍቃድ ያገኘው አገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆነው የሴቶች ስትራቴጂካዊ ማዕከል በይፋ ሥራውን መጀመሩን አስታወቀ ።

በሂልተን ሆቴል በተካሄደው የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተው ስራውን ትናንት በይፋ ያስጀመሩት የሴቶችና ሕጻናት ጉዳዮች ሚኒስትር ወይዘሮ ደሚቱ ሐምቢሳ ናቸው ፡፡

ሚኒስትሯ በዚሁ ጊዜ ባሰሙት ንግግር ማዕከሉ ሴቶችን እስከ ሚኒስትርነት ደረጃ ድረስ የመምራት ብቃት እንዲኖራው ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋጥ በሚደረገው ጥረትም የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ወይዘሮ ደሚቱ አረጋግጠዋል፡፡

የማዕከሉ መሥራችና ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ዶክተር ገነት ዘውዴ በበኩላቸው ፤ “የሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ካልተረጋገጠ ዕድገትና ልማትን ዕውን ማድረግ አይቻልም” ሲሉ ነው ያስገነዘቡት ፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለፃ ማዕከሉ የምርምር ውጤቶችን ለመንግሥት የማቅረብ፣ የሴቶችን የመምራት አቅም ለማሳደግ፣ "ሴቶች አይችሉም" የሚለውን የተዛባ አመለካከት ለመለወጥ ግንዛቤ መፍጠሪያ መርሃ-ግብሮች፣ አዳዲስ የሚወጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና የሴቶችን የኑሮ ጫና በሚቀንሱ ጉዳዮች ላይ በስፋት የሚሰራ ይሆናል።

የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲቻል ማዕከሉን በመደገፍ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት አምባሳደር ዶክተር ገነት ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

"የሴቶች ህገ መንግስታዊ መብት በተለያዩ ሁኔታዎች እየተጣሰ በመሆኑ በዚህ ረገድ ከፍተኛ ሥራ መስራት ይጠበቃል” ያሉት ደግሞ የማዕከሉ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ካሳ ናቸው ፡፡

የሴቶችን ጥያቄ መመለስ የህብረተሰብን ብሎም የሀገርን ጥያቄዎች መመለስ መቻል በመሆኑ ማዕከሉ መቋቋሙ በተለይም የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ከመሆኑም ባሻገር ለፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ተግባራዊነት ትልቅ ዓቅም እንደሚፈጥር ነው ያስገነዘቡት፡፡

በኢትዮጵያ የሐይማኖቶች፣ የብሔሮችና ብሔረሰቦች እንዲሁም የቡድንና የግል መብቶች በሕገመንግስቱ ተከብረው እንደሚገኙ ነው ያስታወሱት አቶ ታደሰ ፡፡

የአምባሳደር ዶክተር ገነት ቤተሰቦች ለማዕከሉ ግማሽ ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውም በዕለቱ ተገልጿል፡፡

በተለያዩ እርከን ደረጃዎች የሚገኙ ሴቶች፣ ምሑራን፣ ነባር ታጋዮች፣ ተመራማሪዎች፣ ተማሪዎች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ከማዕከሉ ጋር በአባልነትና በአጋርነት እየሰሩ እደሆነም ተመልክቷል፡፡

ማዕከሉ ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከልና ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በመተባበር የቴሌዥንና የሬዲዮ ፕሮግራሞችን በቅርቡ ይጀምራልም ነው የተባለው ፡፡

በየሶስት ወሩ የሚታተም “የሕይወት ወግ” በሚል ርዕስ በአማርኛ ቋንቋ መጽሔት ታትሞ እንደተሰራጨም ታውቋል፡፡

ማዕከሉ ሐምሌ 15/2008 ዓመተ ምህረት ተመስርቶ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ቢሮ መክፈቱን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡

በሰለሞን ዓይንሸት