በጎንደር ከተማ በመዝናኛ ስፍራ ላይ የተወረወረ ቦምብ የአንድ ሰው ህይወት ማጥፋቱ የጎንደር ከተማ አስተዳደር የፖሊስ መምሪያ አስታወቀ ።
የፖሊስ መምሪያው ሃላፊ ኮማንደር አሰፋ አሸቤ እንዳስታወቁት ፤በከተማዋ ትናንት ምሽት 12 ሰዓት ማራኪ ክፍለ ከተማ ኢንታሶል በተባለ ሆቴል ላይ ከውጭ የተወረወረው ቦምብ በአንድ ሰው ሞት እና በ18 ሰዎች ላይ ከባድ እና ቀላል የመቁሰል አደጋ አድርሷል።
ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በጎንደር ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ፖሊስ አደጋ አድራሾቹን ለመያዝ ክትትል እያደረገ መሆኑን አመልክቷል ።
"በአከባቢው ፀረ-ሰላም ኃይሎች ከዚህ በፊት ሲከተሉት የነበረው መንገድ ስላላዋጣቸው የጀመሩት አዲስ ስልት ሊሆን ይችላል" ነው ያሉት የመምሪያ ሃላፊው።
ፖሊስ የነዋሪዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ ክትትሉን እና ጥበቃውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል።
ህዝብ የሚገለገልባቸው ተቋማት የፍተሻ እና የክትትል ስራቸውን እንዲያጠናክሩ ነው ያሳሰቡት ።
ህብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት ለፖሊስ እንዲያሳውቅም ጠይቀዋል-(ኤፍ.ቢ.ሲ)።