‹‹በጥልቅ ተሃድሶው ሥልጣንን ለህዝብ ጥቅም ብቻ የማዋል መተማመን ተፈጥሯል›› ጠቅላይ ሚኒስትር

በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴው አመራሩ የመንግስት ሥልጣንን ለሕዝብ ጥቅም ለማዋል ቁርጠኛ አቋም መያዝ እንዳለበት መግባባትና መተማመን እንዲፈጠር ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አስገነዘቡ ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 12ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በመገኘት ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በጥልቅ ተሃድሶ ግምገማው አመራሩ ለህዝብ በመወገን የመንግስትን ሥልጣን ለህዝብ ጥቅም ብቻ በማዋል የተጣለበትን ህዝባዊና መንግስታዊ አደራ እንዲወጣ መተማመን ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡

በጥልቀት የመታደሱ ሂደት አመራሩ ለህዝቡ የሚጠበቅበትን መስዋዕትነት ለመክፍል የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጣ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡

አመራሩ በውጤታማነት እየተለካ በተለያዩ የአመራርነት ቦታዎች ላይ መመደብ እንደሚኖርበት መተማመን መፈጠሩን ነው ያስረዱት፡፡

የአመለካከት መዛባትን በማሰቀረት ፣የዕውቀትና የክህሎት ክፍተቶችን በመሙላት  ግልፅነትና ተጠያቂነትን የተከተለ አሰራር መከተል እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስት ኃይለማርያም ጠቁመዋል፡፡

የአመራሩን ሀብትና ንብረት ለህዝቡ በማሳወቅ የግልፅነትና ተጠያቂነት አሰራር እንዲሰፍን በክትትልና ቁጥጥር ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማትን አቅም የማጠናከር ሥራ መሰራቱን አስገንዝበዋል፡፡

ዜጎች በአመራሮች ሀብትና ንብረት ዙሪያ አስተያየት የሚሰጡበትና የሚተቹበት ሥርዓት እንደሚዘረጋ ተናግረው ለዚህ የሚረዱ መድረኮችም ይዘጋጃሉ ብለዋል-ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴው በኢህአዴግና በአጋር ድርጅቶች መካከል የጋራ መግባቢያ ተፈርሞ ወደ ተግባር በመገባቱ አጋር ደርጅቶች የራሳቸውን በጥልቀት የመታደስ ግምገማ እንዲያካሂዱ ማገዙን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡

የአጋር ደርጅቶችቹ ዋና ዋና አመራሮች በኢህአዴግ ምክር ቤት ጉባዔ ላይ በመሳተፍ በየክልላቸው የ15 ዓመት ጉዞውን በመገምገም የራሳቸውን በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ ጀምረዋል ብለዋል፡፡

ግንባሩ ለአጋር ደርጅቶቹ የፖለቲካ ድጋፍ በማድረግ የሚጠበቅበትን መወጣቱንም አስገንዝበዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስገኛቸውን ፋይዳዎች በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲመልሱ ‹‹ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱ እንዲከበር በማድረግ የህዝቡን ሠላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ አስችሏል ብለዋል ፡፡

በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ከፍተኛ ጉዳት ማስቀረቱን አስታውቀዋል ፡፡ የህዝቡ ማህበራዊ ግንኙነት ወደ ነበረበት እንዲመለስ ጉልህ ሚና መጫወቱንም እንዲሁ፡፡

የሻዕቢያ መንግስትና አጋፋሪዎቹን የመሳሰሉ ፀረ ሠላም ኃይሎች አገሪቱን ለማተራመስ ያደረጉትን ሙከራ መክሸፉን ነው ያመለከቱት ፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የፀጥታ ኃይሎች ለህገ መንግስታዊ ሥርዓቱ ያላቸውን ታማኝነት ያረጋገጡበት አጋጣሚ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመው ችግር ሲከሰት እንዴት ማለፍና ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ትምህርትና ልምድ ለመቅሰም እንደረዳቸው አስገንዝበዋል ፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተወሰኑ ጉድለቶች በስተቀር በጥሩ ሁኔታ እየተተገበረ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት  ሱዳን፣ኬንያ፣ጅቡቲ፣ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳላት አንሰተዋል ፡፡

በተለይም ከጅቡቲ ጋር ከሌሎቹ አገራት አንድ እርምጃ ከፍ ያለ ስትራጂካዊ ግንኙነት ፈጥራለች ነው ያሉት ፡፡

በደቡብ ሱዳን ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍንና በሶማሊያ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ ኢትዮጵያ የበኩሏን ሚና እየተጫወተች መሆኑን ጠቅላይ መኒስትሩ መግለጻቸውን ዋልታ ዘግቧል ፡፡