የፌደራል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈትቤት ባወጣው ሳምንታዊ የአቋም መግለጫው የሀገራችን ኢኮኖሚ ዕድገትና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ስኬቶቹን ለማጠናከርና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሲቪል ሰርቫንቱ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ ነው ያስገነዘበው ።
መንግስት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ሲቪል ሰርቫንቶች የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደታቸውን የሚገመግሙበት የተሃድሶ መድረኮች መዘጋጀታቸው ጠቁሟል።
ይህም መንግስት የጀመረውን የመንግስት ችግሮች በማውጣት በሰፊ ተሳትፎ የተጀመረውን የመታደስ ጉዞ የሚያጎለብቱ ሃሳቦች እንዲያቀርብ እንዲሁም መግባባት እንዲፈጥር ያስችሉታል ነው ያለው ።
በተጨማሪም ሲቪል ሰርቪሱ ጠንካራና ደካማ ጎኖቹን የሚለይበትና ሰራተኛው የሚማማርባቸው በመሆናቸው ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን አስረድቷል ።
መልካም አስተዳደርን ለማስፈን መንግስት ከሚወስዳቸው እርምጃዎች በተጨማሪ ሲቪል ሰርቪሱ የሚሰጠውን አገልግሎት ማሻሻል አንዱና ዋነኛው ተግባር መሆኑን ጠቅሷል ።
ሲቪል ሰርቫንቱ ህዝባዊ ሃላፊነቱን በተሻለ ብቃት እንዲወጣ የተስተካከለ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ሊያሲዘው በሚችል ጥልቅ ተሃድሶ ማለፍ እንደሚኖርበትም አስገንዝቧል ።
በዚህም የተሰጠውን ሃላፊነት ለህዝብ ጥቅም ብቻ እንዲያውል ለማድረግ የሚያስችለው አመለካከት ባለቤት እንዲሆን መድረኮቹ ግንዛቤ ይፈጥሩለታል ነው ያለው መግለጫው ፡፡
እየተካሄዱ ያሉት የተሃድሶ መድረኮች ሲቪል ሰርቫንቱ ህዝብን በግልጽነትና በተጠያቂነት ለማገልገል የገባውን ቃል ለመፈጸም የሚያስችለውን አቅም የሚፈጥርባቸው መሆናቸውንም አስታውቋል።
የተገልጋዩን ህብረተሰብ እርካታ ከማረጋገጥ ባለፈ ስራን ቆጥሮ የመስጠትና መቀበል ባህል በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ በማጎልበት ህብረተሰቡ የሚፈልገውን አገልግሎት ውጤታማ ማድረግ ይቻላል ብሏል መግለጫው።
ስለሆነም ሲቪል ሰርቫንቱ ለሕዝብና ለአገር ያለውን ወገንተኝነት ለማረጋገጥ ስራውን በቅንነት፣ በታማኝነትና በቁርጠኝነት እንዲሁም የአገልጋይነት መንፈስን በመላበስ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ መረባረብ እንዳለብትም አስገንዝቧል ፡፡
ይህም ለመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ወሳኝ ሲሆን ለአገራችን ዕድገት፣ ለህዝቦች አብሮነትና መቻቻል ጠንቅ የሆኑት የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የትምክህት፣ የጥበትና የሃይማኖት አክራሪነትን የመሳሰሉ እኩይ ተግባሮችን ሊዋጋቸው ይገባልም ነው ያለው ።
አገራችን ባለፉት 14 ዓመታት ላስመዘገበችው የኢኮኖሚ ዕድገት እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሲቪል ሰርቪሱ የማይተካ ሚና አበርክቷል፤ እያበረከተም ይገኛል ብሏል።
ከስኬቶቹም ህዝቡ ተጠቃሚ የሚሆንበት ስርዓት በመዘርጋቱ ሲቪል ሰርቫንቱም የዚህ ተጠቃሚ መሆኑን ነው የጠቀሰው ።
ሲቪል ሰርቫንቱ ዓላማውን በማንገብ ተልዕኮዎችን መወጣት ከቻለ፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እልባት ከመስጠት ባለፈ የዴሞክራሲ ስርዓቱም በማጎልበት የተጀመሩ የልማት ስራዎችም ይፋጠናሉ ብሏል።
ሲቪል ሰርቫንቱ ህይወቱም በዘላቂነት ለመቀየር በመካሄድ ላይ ባሉት የተሃድሶ መድረኮች በንቃት በመሳተፍ ለመልካም አስተዳደር መጎልበት የበኩሉን ሚና መወጣት ይኖርበታል ሲል ጥሪውን አስተላልፏል።