ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር ለመወያየት መዘጋጀታቸውን ገለጹ

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየትና ለመደራደር መድረኮች ማዘጋጀቱ የአገራዊ ዕድገት ቀጣይነት እንዲኖረው  ሚናው የጎላ መሆኑን ፓርቲዎች ገለጹ።   

የኢፍዴኃግ፣ የቅንጅት፣ የኢዴፓና የኢዴአን ፓርቲዎች ተወካዮች እንደገለጹት፤ ኢህአዴግ ለፓርቲዎቹ በሚያዘጋጀው መድረክ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችላቸውን መሰረታዊ የመከራከሪያ ነጥቦች ለይተዋል።

የኢትዮጵያ ፍትህና ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ግንባት (ኢፍዴኃግ) ሊቀመንበር አቶ ገረሱ ገሳ እንዳስታወቁት፤ ኢህአዴግ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሊያሳትፍ የሚችል የድርድርና የውይይት መድረኮች ማዘጋጀቱ መልካም ነው።

በመድረኩም አገራዊ ጉዳዮችን በማንሳት ለመወያየትና ችግሮች ለመፍታት እንደሚያስችል አመልክተው፤ “ፓርቲዎችም የራሳቸው አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ያግዛል” ነው ያሉት።

“አገሪቷ ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች በመሆኑ የዚህን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ዕድገቷን የሚፈታተኑ ጉዳዮች ለማቃለል ከገዢው ፓርቲ ጋር መምከርና መደራደር ያስፈልጋል” ብለዋል አቶ ገረሱ።

ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለአገር እድገትና ለውጥ የሚቀርቡትን የመደራደሪያ ሀሳቦች እውቅና እንዲሰጥም አቶ ገረሱ ጠይቀዋል።

የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (ቅንጅት) ሊቀመንበር አቶ አየለ ጫሚሶ በበኩላቸው፤ የአገሪቷ ህገ-መንግሥት “የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲኖር ዕድል ፈጥሯል” ነው ያሉት።

ተፎካካሪ ፓርትዎችም የአገሪቷን ልማትና እድገት አስመልክቶ ዓላማና ግብ አስቀምጠው፣ ዕቅድ ቀርጸው የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው “በጋራ የአገሪቷ ጉዳዮች ላይ የጋራ የውይይትና የክርክር መድረኮች ሊኖራቸው ይገባል” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ገዢው ፓርቲ ለዚህ ዓይነት ‘መድረክ ዝግጁ ነኝ’ ማለቱን ፓርቲያቸው እንደሚደግፍ ጠቁመው፤ በዚህም ፓርቲያቸው የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ  ዝግጁ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ባልከው እንደተናገሩት፤ ፓርቲው ከዚህ በፊት ከገዢው ፓርቲ የጋራ መድረኮች እንዲኖሩ ፍላጎት ነበረው።

በአሁኑ ወቅት ገዢው ፓርቲ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚያሳትፉ የውይይትና የድርድር መድረኮችን ማዘጋጀቱ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግሥት ለውይይቱና ድርድሩ ተግባራዊነት ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሚገባም ነው አስተያየት የሰጡት።

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ (ኢዴአን) ሊቀመንበር አቶ ጎሹ ገብረሥላሴ ከተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለሚደረጉ ውይይቶችና ድርድሮች ፓርቲው የመወያያ ሀሳቦችን ለመንግሥት ማቅረቡን ገልጸዋል።

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የድርጅቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፤ ድርጅቱ እንደ ገዢ ፓርቲ በጋራ ከመሥራት አኳያ የነበረበትን ውስጣዊ ክፍተት በመለየት በአገራዊ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ይበልጥ ተቀራርቦ ለመሥራት መዘጋጀቱን መግለጻቸው ይታወቃል ፡፡(ኢዜአ)።