ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከህብረተሰቡ ከሚጠበቀው የግንባታ ወጪ 70 በመቶ መሰብሰቡን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ ፡፡
የምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አብርሃም ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከሕብረሰተሰቡ የሚጠበቀው 12 ነጥብ 6 በመቶ የግንባታ ወጪ ውስጥ እስከላሁን ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን ገንዘብ ማሰባሰብ ተችሏል፡፡
በላፈው በጀት ዓመት መጨረሻ ከሕብረተሰቡ የተሰባሰበው 8ነጥብ7 ቢሊየን ብር እንደነበረ አቶ ኃይሉ አስታውሰው፤ አሁን ላይ 9 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰብ እንደተቻለ ነው ያስታወቁት ፡፡
በተመሳሳይ ከዳያስፖራው የተሰባሰበው የሐብት መጠን ወደ 30 ሚሊየን ዶላር አካባቢ ደርሷል ነው ያሉት ፡፡
በታሕሳስ ወር ብቻ ከ1ሺህ በላይ ዜጎች ግድቡን እንደጎበኙትና በቀጣይ ለሚያደርጉት ተሳትፎና ጠንካራ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚደረገው ጥረትም ተጠናክሮ እንቀጠለም ገልጸዋል፡፡
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በሶስት ፈረቃ ለ24 ሰዓት ያህል ሳይቋረጥ እየተገነባ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ግንባታው በሐምሌ 30/2008 ዓመተ ምህረት 52 በመቶ እነደነበረ አቶ ኃይሉ አስታውሰው፣ በጥቂት ወራት 58 በመቶ ማድረስ መቻሉ ግንባታው በፍጥነት እየተከናወነ ለመሆኑ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡