ኢትዮጵያና ጊኒ ስትራቴጂያዊ አጋርነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ

ኢትዮጵያና ጊኒ ስትራቴጂያዊ አጋርነታቸውን ለማሳደግ የጀመሯቸውን ጥረቶች አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በዳቮስ ስዊዘርላንድ ከጊኒው ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ ጋር በሁለትዮሽና አህጉራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

መሪዎቹ ንግድና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ የሃገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

ባለፈው ሚያዚያ ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጊኒን በጎበኙበት ወቅት ሃገራቱ 20 ስምምነቶችን መፈራረማቸው ይታወሳል።

መሪዎቹ ሃገራቱ የደረሷቸውን የጋራ ስምምነቶች ገቢራዊ ማድረግ በሚቻልበት ዙሪያ መክረዋል።

ፕሬዚዳንት ኮንዴ እንደገለጹት፤ ጊኒ በታዳሽ ኃይል ማስፋፋት፣ በግብርና ዘርፍና እና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ከኢትዮጵያ ልምድ መቅሰም ትሻለች።

በተለይ በታዳሽ ኃይል ልማት ያላት አቅምና ልምድ ለአፍሪካውያን ሞዴል ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ፤ በዚህ መስከ ሃገራቸው የኢትዮጵያን ድጋፍ ትሻለች ብለዋል።

በቅርቡም አንድ የጊኒ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልኩም ተናግረዋል፤ ሃገራቸው በፀረ-ሽብር ትግል ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት የመስራት ፍላጎት እንዳላት በመጥቀስ።

ፕሬዚዳንቱ አፍሪካ እየገጠማት ያለውን የሠላምና ፀጥታ ችግር በራሷ አቅም መፍታት እንድትችል፤ ጊኒ ከኢትዮጵያ ጋር ተባብራ እንደምትሰራም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጉዳዮች እየተጫወተች ያለችውን ሚና ፕሬዚዳንቱ አድንቀው፤ በዚህ ረገድ ሃገራቸው ተሞክሮ ለመጋራት ፍላጎት አላት ነው ያሉት።

ሁለቱ መሪዎች የአፍሪካ ኅብረት ተጠናክሮ መቀጠል በሚችልበት ሁኔታ ዙሪያም ምክክር አካሂደዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ያላትን ልምድ ለጊኒ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል-(ኢዜአ)።