ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የበሩባቸውን ድክመቶች አስወግደው የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የፌደራል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈትቤት አስገነዘበ ፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ከመሥራት አኳያ የነበሩባቸውን ድክመቶች አስወግደው በሚዘጋጁት መድረኮች የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የአገሪቷን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለማገዝ ቁርጠኝነታቸውን ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው ጽሕፈትቤቱ ባወጣው ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ አስገንዝቧል ።
ዜጎች በፈለጉት የፖለቲካ ድርጅት ታቅፈው መንቀሳቀስ የሚችሉበት፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት ወሳኝ ሚና ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ተመስርተው በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ መፈጠሩን በመጥቀስ ።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገሪቷ በተካሄዱ ምርጫዎች ሁሉ እየተካፈሉ የሚገባቸውን ያህል የምክር ቤት ወንበሮች ሲይዙ መቆየታቸውንም አንስቷል ፡፡
ይሁንና ባለፉት ሁለት ምርጫዎች የገዢው ፓርቲ ሙሉ የበላይነት የተከሰተበት በመሆኑ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሳትፎ ተገድቦ እንደነበር አመልክቷል ።
በመሆኑም መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ተረጋግቶ እንዲቀጥል ካለው ፍላጎት በመነሳትና በአገሪቷ ያለውን የፍላጎት ብዝሃነት ይገነዘባል ነው ያለው መግለጫው ፡፡
ስለሆነም ወሳኝ የሥልጣን አካል የሆኑት የህዝብ ምክር ቤቶችን የተለያዩ ድምጾች የሚሰማባቸውና የሚፎካከሩባቸው መድረኮች ማድረግ እንደሚገባ አቋም መውሰዱን በማስታወስ ።
ይህም መንግስት ዴሞክራሲያዊ መድረኮችን በማስፋት በሰላማዊ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ውይይት፣ ድርድርና ክርክሮች ማካሄድ ብሎም ህጎችን እስከማሻሻል ድረስ መሄድ እንዳለባቸው ቁርጠኝነቱን ማሳየቱን ነው የጠቀሰው ።
ከዚህ አንጻር ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰላማዊ እስከሆኑ ድረስ የሚሳተፉባቸውን መድረኮች እያመቻቸ መሆኑን አስረድቷል ።
ዛሬ አገሪቷ የምትመራበትን ህገ መንግሥት በማርቀቅ ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎች የየራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን እንደማይዘነጋ በመግለጽ ።
አገሪቷ የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መከተል ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቧን መግለጫው አውስቷል።