Skip to content
የአርብቶ አደር ተወካዮች ከመንግስት የበላይ አመራሮች ጋር በአገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚወያዩ የፌደራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታወቀ
የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበበ ወርቁ ለዋልታ እንደገለጹት ፤በግጅጅጋ ከተማ 16ኛው የአርብቶ አደሮች በዓል “የአርብቶ አደሩ የሰላምና የልማት የላቀ ተሳታፊነት ተጠቃሚነት ለህዳሴያችን በሚል መሪ ሃሳብ ከጥር 15 እስከ 17/2009 ዓመተ ምህረት ይከበራል ፡፡
በዚሁ በዓል ላይም በአርብቶ አደሩ የልማት ፣የሰላም ፣የዲሞክራሲ ግንባታ ዙሪያ ላይ የጋራ ምክክር የሚያደርጉበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
መንግስት በአርብቶ አደሩ ያሉ ክፍተቶችን ከአርብቶ አደሩ አስተያየት በማዳመጥ ለቀጣይ የተሻለ ሰላም፣ልማት ዲሞክራሲ ግንባታ በግብኣት ለመሰብሰብ እንደሚረዳው ነው ያመለከቱት ፡፡
ከውይይቱ በኋላም አርብቶ አደሮች የመንግስትን ቀጣይ አቅጣጫዎችን የጋራ ግንዛቤ የሚይዙበት መሆኑን አብራርተዋል ፡፡
በተጨማሪም የፓናል ውይይት በዩኒቨርሲቲዎች የተካሄዱ በአርብቶ አደር ዙሪያ ላይ ያሉ ጥናቶች ይቀርቡና ውይይት ይካሄድባቸዋል ብለዋል ፡፡
ባህላዊ በኢትዮጵያ ሶማሌ፣በዓፋር ፣በደቡብና በኦሮሚያ አርብቶ አደር አከባቢ የተዘጋጁ ስፖርታዊ ትርዒቶች እንደሚቀርቡም ጠቁመዋል ፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ በ14 እስከ 18/2009 ዓም በሚቆየው የኤግዚብሽንና ባዛር በአርብቶ አደሩ አከባቢ መንግስት ያከናወናቸው ዋና ዋና ስራዎች እንደሚቀርቡ ገልጸዋል፡፡
እንደዚሁም ለጋሽ፣ ልማታዊ ድርጅቶችና ማህበራት ምርቶቻቸውም የሚያቀርቡበት ይሆናል ብለዋል፡፡
በክልሉ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ለሌሎች አርብቶ አደር ማህበረሰብ ፣ ጥሩ ተሞክሮ የሚሆኑ የመስክ ምልከታ እንደሚኖርም ጠቁመዋል ፡፡