ደኢህዴን ከ1ሺህ500 በላይ ነባር አመራሮችን ከኃላፊነት እንዲነሱና እንዲሸጋሸጉ ማድረጉን አስታወቀ

የመጀመሪያውን ጥልቅ የተሀድሶ ንቅናቄ መሰረት በማድረግ አመራሩን መልሶ የማደራጀት ሥራ ማጠናቀቁን የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ አስታውቋል ።

የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ድርጅቱ ከ1 ሺህ 500 በላይ ነባር አመራሮችንም ከነበሩበት የኃላፊነት ቦታ እንዲነሱና እንዲሸጋሸጉ ማድረጉንም አስታውቋል።

በዚሁም መሰረት 910 አመራሮች ከኃላፊነታቸው የተነሱ ሲሆን፤ 612 አመራሮች የአፈጻጸም ውጤታቸው ታይቶ  እንዲሸጋሸጉ መደረጉን አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል።

በዚህም ኃላፊነት በማይሰማቸው አመራሮች ተይዞ ከነበረው ከ6 ሺህ ሄክታር በላይ የገጠር መሬት ውስጥ 3 ሺህ ሄክታሩን ማስመለስ እንደተቻለ አረጋግጠዋል።

እንዲሁም ተመዝብሮ ከነበረው 32 ሚሊዮን ብር ውስጥ 11 ነጥብ 7 ሚሊዮኑን ማስመለስ መቻሉንም ጠቁመዋል።

እንድ አቶ ተስፋዬ ገለጻ፣ 87 አመራሮች ህጋዊ ያልሆነ ሰነድ ተጠቅመው በመገኘታቸው ተገቢ እርምጃ እንዲወሰድባቸው በሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

በክልሉ ላለፉት ሦስት ወራት ሲካሄድ የነበረው በመጀመሪያው የጥልቅ ተሃድሶ የንቅናቄ ምዕራፍ ከ10 ሺህ 500 በላይ ከፍተኛ አመራሮችና 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን የድርጅቱ አባልና ደጋፊዎች ተሳትፈዋል ነው ያሉት ።

የመጀመሪያውን በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ውጤታማነት መሰረት በማድረግ አመራሩን በግምገማ አጥርቶ ዳግም የማደራጀት ሥራ በአሁኑ ወቅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው እንደገለጸው፤በክልሉ ከ1 ሺህ 500 በላይ አዳዲስ አመራሮችን ወደ ኃላፊነት መጥተዋል ፡፡

በመጀመሪያው ንቅናቄ የእድገትና የለውጥ ጉዞ ከአመራሩ እስከታችኛው የድርጅቱ አባላት ድረስ መድረኮች መካሄዳቸውን ገልጸዋል።

"ከሕዝብ ጋር በተደረገው ውይይትም በተከናወኑ ሥራዎችና በገጠሙ ችግሮች ላይ በጥልቀት በመወያየት የጋራ መስማማት ላይ ተደርሷል።" ብለዋል።

ሙስናና ብልሹ አሰራር፣ ከመሬት አስተዳደር የተያያዙ ችግሮች፣ የመንግስት ሃብትን በአግባቡ አለመጠቀም፣ አርኪና ቀልጣፋ አገልግሎት አለመስጠት እንዲሁም መልካም አስተዳደርን አለማስፈን በንቅናቄው እንደ ጉድለት መነሳታቸውን አቶ ተስፋዬ አረጋግጠዋል።

ክልሉ ባለፉት 15 ዓመታት ባለሁለት አሃዝ ምጣኔ ሃብት ማስመዝገቡንና በተለይም በኢኮኖሚ ልማት ከዕለት ጉርስ አልፎ ለገበያ የሚያቀርብ አርሶ አደር ማፍራት መቻሉን ጠቅሰዋል።

በማህበራዊ ልማትም በትምህርት፣ በጤናና በመሰረተ ልማት ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ ዕድገት መታየቱን ሕብረተሰቡ በተወያየባቸው መድረኮች ላይ የጋራ ድምዳሜ መደረሱን ገልጸዋል።

በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ አንደኛው ምዕራፍ ተጠናቆ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ መሸጋሩንም ነው ያስታወቁት ።

ሁለተኛ ዙር በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ  በተግባር አፈጻጸም መለውጥ ላይ የሚያተኩር መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፣ ለ1 ሺህ 200 አዳዲስ አመራሮች ከነገ በስቲያ  ጀምሮ የሥራ አመራርና ስልጠና እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል-(ኢዜአ)።