ኢጋድ በምስራቅ አፍሪካ አገራት ድንበር አካባቢዎች የልማት ፕሮጀክት መጀመሩን አስታወቀ

የምስራቅ አፍሪካ የልማት  በየነ መንግሥታት ድርጅት ( ኢጋድ )  ድርቅን በዘላቂነት  ለመከላከልና  የአርብቶ አደር ማህብረሰብን  የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል የሚያስችል   መርሃ ግብር በተለያዩ  የምስራቅ  አፍሪካ  አገራት  የጋራ ድንበር አካባቢዎች  መጀመሩን  አስታወቀ ።    

ለልማት ፕሮጀክቱ  ተግባራዊነት  የአውሮፓ ህብረት  የገንዘብ ድጋፍ  ያደረገ ሲሆን  የለጋሽ አገራትና  የኢጋድ አባል አገራት ሚኒስትሮች  በተገኙበት በአገራቱ  የአርብቶ አደሩን  የሚያሳትፈው  ፕሮጀክት  የመጀመሪያ  ምዕራፍ በሚተገበርበት ሁኔታ ላይ በአዲስ አበባ  ውይይት መካሄድ ተጀምሯል ።

የኢጋድ  አባል አገራት  በአርብቶ አደሩ ልማት ላይ በጋራ ለመሥራት  የተስማሙ መሆኑ ተገልጿል  ።

ለፕሮጀክቱ  የመጀመሪያ ምዕራፍ  ትግበራም 60 ሚሊዮን ዩሮ ተለቋል ።    

የኢጋድ ዋና ፀሓፊ መሃቡብ ማሊም እንደገለጹት ኢጋድ  በአባል  አገራት  ድንበር  አካባቢዎች  የአርብቶ አደር ህይወትን ለማሻሻል ከተለያዩ  የልማት አጋሮች  ጋር በመሆን  እየሠራ ይገኛል ።

 እንደ  መሃቡብ ገለጻ የኢጋድ አገራት ድንበር በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የሚገኙትን አርብቶ አደር ማህበረሰቦች በተደጋጋሚ ለድርቅ ተጋላጭ  የሚሆኑበት ሁኔታ ስላለና  የአገራቱ የአርብቶ አደር ማህበረሰብ ድህነትን  ለመቅረፍ እንዲሁም  የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን  ለማጎልበት  በጋራ  የሚሠሩት ሥራዎች እየተጠናከሩ መጥተዋል ።                     

አሁን  የተጀመረው   የአርብቶ አደር ልማት ፕሮጀክት  የአካባቢውን አገራት ግንኙነት በማሻሻል  ግጭትን  በማስወገድ  ዘላቂ  ሰላምን  በማረጋጋጥ  በኩል  የበኩሉን  ሚና ይጫዋታል ።

የእንስሳትና አሳ ሃብት ልማት  ሚኒስትር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በበኩላቸው እንደገለጹት  ፕሮጀክቱ   በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚያገጥሙ መሰናክሎችን  በማለፍ አቅምን የሚያሳደግና  የአርብቶ  አደሩን ፍላጎት  የሚያሟሉ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ይረዳል  ።

እንደ ፕሮፌሰር  ፍቃዱ ማብራሪያ  የኢጋድ አባል አገራት በአንስሳት ሃብት ምርታማነትን እንዲያሳድጉና  በአርብቶ አደር አካባቢ ኢንቨስትመነት ለማስፋፋት የሚያካሄዱትን ሥራዎች እንዲቀጥሉ  እገዛ ይኖረዋል ።

በኢትዮጵያ  ባለፈው ዓመት በአየር  መዛባት   ምክንያት  ከ10  ሚሊዮን ህዝብ በላይ ለአስቸኳይ ጊዜ  እርዳታ የተዳረገች ቢሆንም  አገሪቱ  ችግሩን እየመከተች ከመሆኗም ባሻገር  ለአየር ንብረት  ለውጥ የማይበገር  የአረንጓዴ ኢኮኖሚን በመግንባት ዘላቂ ልማት ለማረጋጋጥ እየሠራች መሆኑን አስረድተዋል  ።

( ትርጉም : በሰለሞን ተስፋዬ)