የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበት 6ኛ ዓመትና 41ኛው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) በታላቅ ሩጫ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተገለጸ፡፡
የሴቶችና ሕፃናት ጉዳዮች ሚኒስትር፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ እና የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ዛሬ በሸራተን አዲስ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተመለከተው ሁለቱን ድርብ በዓላት ከ650 ሺህ በላይ ሰዎችን በሚያሳትፍ ሩጫ በድምቀት ለማክበር ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ ነው፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እውን መሆን በተለይም ሴቶችን በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ ዘርፎች በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸውና አሁን ያለባቸውን ጫና በማቃለል ኑሮአቸውን ለመቀየር ጉልህ ድርሻ እንዳለው የሴቶችና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት ገልጸዋል፡፡
አክለውም በሩጫው የሴቶች ክብር፣ ፍቅርና አክብሮት የሚገለጽበት በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በሩጫው ላይ በመሳተፍ አጋርነቱን ሊያሳይ ይገባል ብለዋል፡፡
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረሥላሴ በበኩላቸው እንደገለጹት ለሕዳሴውን ግድብ ሕብረተሰቡ እያከናወነው ያለውን ጠንካራ ተሳትፎና ሀገራዊ መግባባትን ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ለማገዝ ሩጫው ጉልህ ድርሻ አለው፡፡
በተጨማሪም ሩጫው ሥፖርታዊ ውድሮችን ሕዝባዊ መሰረት እንዲኖራቸው ለማገዝና የከተሞች ጽዳትና የአረንጓዴ ውበት አገርአቀፍ ልማትን እውን ለማድረግ የሚያግዙ ታላላቅ ግቦችን ያቀፈ እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡
ሩጫው 6 ኪሎሜትር እንደሚሸፍንና በሁሉም የክልል ከተሞችና የከተማ አስተዳደሮች የካቲት 26 እንደሚከናውን ታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ብቻ ከ100ሺህ በላይ ዜጎችን በሩጫው ለማሳተፍ ታቅዷል፡፡
ሩጫው “የሴቶች የቁጠባ ባሕል ማደግ ለሕዳሴያን መሰረት ነው!” እና “ጊዜ የለንም እንሮጣለን ለሕዳሴ ግድባችን እንቆጥባለን!” የሚሉ መርሆችን የነገበ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡
ሞዴል ሴት ቆጣቢዎች፣ ከዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው የራሳቸውን ሥራ እየሰሩ ለሌሎችም ሰፊ የስራ ዕድል የፈጠሩ ሴቶች፣ ለሴቶች ሕይወት መቀየር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ግለሰቦችና ድርጅቶችም የዕውቅናና ሽልማት እንደሚበረከትላቸውም ተመልክቷል፡፡
ወርሃ የካቲት ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚሆን የቦንድ ሽያጭ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞችም የሚከናወኑበት እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
እስካሁን ከሕብረሰተሰቡ የሚጠበቀው ከ12 ነጥብ 4 እስከ 12 ነጥብ 6 በመቶ የግንባታ ወጪ ከ70 በመቶ በላይ ወይም 9 ቢሊየን ብር በላይ ማሰባሰብ ተችሏል፡፡
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 58 በመቶ እንደተከናወነ ፡፡
በዚሁ መድረክ ሴት አመራሮች፣ የሙያ ማሕበራት ተወካዮች፣ የሴት አደረጃጀቶች፣ የመከላከያና የፖሊስ ኮሚሽን ተወካዮች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና ታዋቂ አትሌቶች መካፈላቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡