ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጅግጅጋ ለሚከበረው የአርብቶ አደሮች ቀን ወደ ስፍራው አቅንተዋል

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለ16ኛው የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች ቀን የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀብሪ ደሃር አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሃመድ እና የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በዓሉ ነገ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጅግጅጋ ይከበራል ።

ቀኑ “የአርብቶ አደሩ የሰላምና የልማት የላቀ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለህዳሴያችን” የሚል መሪ ቃል ያለው ሲሆን ፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ የልማት ተቋሞችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል ።

እንደዚሁም የበዓሉ አካል የሆነና ከአራቱ የአርብቶ አደር ክልሎች የተውጣጡ ተሳታፊዎች በክልሉ የተመረጡ ወረዳዎችና ማዕከላት የመስክ ጉብኝት እያደረጉ ነው።

ከበዓሉ ቀደም ብሎ የተከፈተው አውደ ርዕይና ባዛርም እየተካሄደ ይገኛል።

የአራቱ አርብቶ አደር ክልሎች የሆኑት፥ የኦሮሚያ፣ የአፋር፣ ሶማሌ እና ደቡብ ክልል ተወካዮችም የየክልላቸውን ተሞክሮ አቅርበው ውይይት አድርገዋል።

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ከ88 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የእንስሳት ማቆያ ኳራንቲን ጎብኝተዋል ።

የፌደራል ጉዳዮችና የአርብቶ አደር አካባቢ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ካሳ ተክለብርሃን፤ መሰል የአገልግሎት መስጫ ተቋማት በሁሉም የአርብቶ አደር አካባቢዎች እንዲቋቋሙ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

ማዕከሉ አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር፤ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ በማሳደግ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዝ አስረድተዋል ።

በ54 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ማዕከል፤ ዓለም አቀፍ ህግ የሚጠይቀውን የንጽህናና የህክምና ማረጋገጫ ያሟላ ነው ተብሏል።

ከ32 ሺህ በላይ እንስሳትን በ21 ቀናት ውስጥ በመመርመር ወደ ውጭ ገበያ መላክ እንደሚያስችልም ተገልጿል።

ውሀና ቤተ ሙከራዎች ከገቡለት በኋላ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ስራ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል-(ኤፍ.ቢ.ሲ)።