በደሴ ከተማ የሸዋ በር መስጅድ የሃይማኖት አባት የሆኑት ሼህ ኑሩ ይማምን በሽጉጥ በመምታት ህይወታቸው እንዲያልፍ በማድረግ የተከሰሰሱት ግለሰቦች ላይ እስከ 16 ዓመተ የሚደርስ ቅጣት መወሰኑን የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ ።
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ በዋለው ችሎት 13ቱ ተከሳሾች ላይ የእስር ቅጣት አስተላልፏል ።
ተከሳሾቹ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት እና አላማቸውን የማይደግፉ አካላት ላይ የሃይል እርምጃ ለመወሰድ ሲንቀሳቀሱ ነበር ተብለው በተመሰረተባቸው የሽብር ወንጀል ክስ ባለፈው የችሎቱ ውሎ የጥፋተኝነት ብይን ተሰጥቶባቸዋል።
ጥፋተኛ የተባሉት ተከሳሾች 1ኛ አህመድ እንድሪስ፣ 2ኛ አንዋር ኡመር፣ 3ኛ ሷሊህ መሃመድ፣ 4ኛ አደም አረጋውያን ጨምሮ አስራ ሶስት ተከሳሾች ናቸው።
የአቃቤ ህግ ክስ እንደሚያመላክተው ተከሳሾቹ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ አክራሪነትን ለማስፋፋት በመደራጀት እስላማዊ መንግስት ለመመስረት ተንቀሳቅሰዋል።
በሰኔ 27 ቀን 2005 ከምሽቱ 2 ስዓት በደሴ ከተማ የሸዋ በር መስጅድ የሃይማኖት አባት የሆኑት ሼህ ኑሩ ይማምን በሽጉጥ ግንባራቸው ላይ ሁለት ጊዜ በመምታት መግደላቸውም በክስ መዝገባቸው ላይ ተመላክቷል።
በተለያዩ ጊዜያትም የእነሱን አላማ የማይደግፉ ግለሰቦች ላይ የሃይል እርምጃ ለመውሰድ መንቀሳቀሳቸውም በክሱ ተጠቅሷል።
የግራ ቀኙን ክርክር ሲያደምጥ የቆየው የልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በተከሳሾቹ ላይ ከ3 አመት እስከ 16 አመት የጽኑ እስራት ቅጣት አሳልፏል።
በዚህም 8ኛ ተከሳሽን በ16 አመት ፅኑ እስራት፣ 1ኛ፣ 3ኛ፣ 4ኛ እና በ15 እንዲሁም 7ኛ ተከሳኝን በ15 አመት ከ6 ወር፣ 6ኛ እና 11ኛ ተከሳሾችን ደግሞ በ14 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።
2ኛ ተከሳሽን ደግሞ በ12 አመት ፅኑ እስራት፣ 5ኛ እና 12ኛ ተከሳሾች ደግሞ በ6 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አሳልፏል።
ከዚህ ባለፈም 10ኛ ተከሳሽ በ5 አመት፣ 14ኛ ተከሳሽ 4 አመት ከ4 ወር እንዲሁም 13ኛ ተከሳሽን ደግሞ 3 አመት ከ8 ወር እንዲቀጡ ውሳኔ አሳልፏል-(ኤፍ.ቢ.ሲ)።