"እኛ በዓባይ የተቆራኘን ስለሆነ ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ጋር በቅርበት እንሰራለን" ሲሉ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገለጹ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የግብፅ አቻቻውን ሳሜህ ሽኩሪን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
ሳሜህ ሽኩሪ በዚሁ ጊዜ "እኛ ከኢትዮጵያውያን እህቶች እና ወንድሞቻችን ጋር በቅርበት እንሰራለን፤ እኛ በታሪክ ተቆራኝተናል፣ በዓባይ ተቆራኝተናል፤ ይህንን ግንኙነት በጋራ ከሠራን እናስቀጥለዋለን" በማለት እምነታቸውን ገልጸዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት እየተጠናከረ የመጣና ቀጣይነት ያለው መተማመንን የተላበሰ አጋርነት ነው ብለዋል ።
የግብጽ የአፍሪካን የፖለቲካና የልማት ችግሮች ለመፍታት ኢትዮጵያ እና ግብፅ በጋራ እንዲሰሩ ሳሜህ ሽኩሪን ጠይቀዋል፡፡
ይህም አጋርነት በየሀገራቱ መካከል ያለውን የልማት ግብ ለማሳካት፣ ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ እንደሚረዳ ገልጸው በአፍሪካ ደረጃ የሚስተዋሉ ችግሮችንም ለመፍታት እጅ ለእጅ መስራት አለብን ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ የሀገራቱን ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ለማድረግ አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ለግንኙነቱ ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ይህን የጋራ ግንኙነት አሁን ካለበት ይበልጥ ለማጎልበት ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር ተቀራርበው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።
ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው ከግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ ጋር ያደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት የሀገራቱን ግንኙነት የሚያጠናክር እንደሆነ ገልጸዋል-(ኢዜአ)።