28ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ከስዓታት በኋላ ይከፈታል።
በመሪዎች ደረጃ በሚካሄደው ጉባኤ የህብረቱ አባል ሃገራት መሪዎችንና የመንግስታቱን ድርጅት ዋና ፀሃፊ ጨምሮ ተጋባዥ እንግዶች ይሳተፋሉ።
የጉባኤው መርሃ ግብር አንደሚያሳየው፥ ያለፈውን አንድ ዓመት የአፍሪካ ህብረትን በሊቀ መንበርነት የመሩት የቻዱ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ ጉባኤውን በንግግር ይከፍታሉ።
ተሰናባቿ የአፈሪካ ህብረት ኮምሽን ሊቀ መንበር ዶክተር ኒኮ ሳዛና ድላሚኒ ዙማም የመጨረሻ ንግግራቸውን በህብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ያደርጋሉ።
የተባበሩት መንግስታት ደርጅት ዋና ፅሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝም በህብረቱ ንግግር ከሚያደርጉት እንግዶች መካከል ናቸው።
የህብረቱ አባል ያልሆኑ ሁለት ተጋባዠ እንግዶችም በህብረቱ ጉባኤ ላይ ንግግር የሚያደርጉ ሲሆን፥ በተደጋጋሚ በህብረቱ በመገኘት የሚታወቁት የፍልስጤሙ መሪ ሙሃሙድ አባስ አንዱ ናቸው።
የጊኒው ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ አዲስ አበባ በሚካሄደው በጉባዔው የኅብረቱን የሊቀመንበርነት ቦታ ከቻዱ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ ይረከባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የመሪዎቹ ጉባኤ በቀጣይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንን በሊቀ መንበርነት ለመምራት በእጩነት ከቀረቡት አምስት ተፎካካሪዎች አንዱን ይመርጣሉ።
የህብረቱ ምክትል ኮምሽነር ስምንት የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤቱ ምርጫም ይካሄዳል።
ሞሮኮ ዳግም ወደ ኅብረቱ ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄም በመሪዎች ጉባኤ ላይ ውሳኔ ይሰጥበታል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)