ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከግብ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ ኤል ሲሲ ጋር መከሩ።
ከ28ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እና ፕሬዚዳንት ኤል ሲሲ የተናጠል ውይይት ያደረጉት።
ሁለቱ መሪዎች በአምስት ነጥቦች ላይ ውይይት በማድረግ የጋራ አቋም ይዘዋል።
መሪዎቹ በሀገራቱ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር እስካሁን የተገኙ መልካም ዲፕሎማሲያዊ ድሎችን ለማጉላት እንደሚጠቅሙና የሁለትዮሽ መተማመን ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተስማምተዋል።
ሁለትዮሽ ቀጠናዊ የትብብር መስኮችን ማስፋት እና ማጠናከር በተለይም በፖለቲካ፣ ሰለማና ፀጥታ፣ በኢኮኖሚ ዘርፍ ያሉ ትብብሮችን ማጉላት እንደሚገባ፤ ሁለትዮሽ ግንኙነትና ወንድማማችነትን የሚጎዳ ማንኛውንም አይነት ክስተት መቆጣጠርና መገደብ እንደሚገባም ነው ከስምምነት ላይ የደረሱት።
መሪዎቹ ታላቁ የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ የሶስትዮሽ የቴክኒክ ኮሚቴ ውይይቶችን እየተከታተለ እንደሆነና ግድቡን አስመልክቶ ያላቸውን በትብብር መንፈስ የመስራት ቁርጠኝነት አድሰዋል።
የመረጃ ልውውጥን ማሳደግ፣ የሁለትዮሽ ግንኙነትንና የጋራ ጉዳይ በሆኑ ቀጠናዊ እና አለማቀፋዊ ጉዳዮች በመሪዎች እና በተቋማት ደረጃ ተከታታይነት ያለው ምክክር እንዲካሄድም መሪዎቹ ተስማምተዋል።
ከዚህም ባለፈ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና በህዝቦች መካከል መተማመንን ለማሳደግ እንደሚያስፈልግ ለዚህም የመገናኛ ብዙሃን ሚና ወሳኝ መጫወት እንዳለባቸው ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም እና ፕሬዚዳንት ኤል ሲሲ የተስማሙት።
መሪዎቹ በቋሚነት በተለያየ ጊዜ በሁለቱ ሀገራት ጉብኝት እንደሚያደርጉም ከመግባባት ላይ ደርሰዋል።
በዚህ አጋጣሚም ፕሬዚዳንት ኤል ሲሲ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም በቅርቡ በግብፅ ጉብኝት እንዲያደርጉ ጋብዘዋቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ከሱዳን ፕሬዚዳንት ሀሰን አል በሽር ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
የረጅም ጊዜ ግንኙነት ያላቸው ኢትዮጵያ እና ሱዳን በንግድ እና ኢንቨስትመንት እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
ሁለቱ ሀገራት ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ግንኙነታቸውን ለማሳደግም ተስማምተዋል-(ኤፍ.ቢ.ሲ) ፡፡