የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ እና የድርጅቱ የእርዳታ ዋና ኃላፊ ስቴፈን ኦብራይን እንደገለጹት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከል ለሚወስደው እርምጃ ድጋፍ እንዲሠጥ ጥሪ አድርገዋል ።
በየትኛውም የዓለም አካባቢ ለሚከሰት ድርቅ ምላሽ መሥጠት በጎ ምግባር ሥራ ብቻ ሳይሆን ፍትሃዊነትና የዓለም ጥቅምን የማስከበር ጉዳይ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ባለው በ28ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተገኙት አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጠቁመዋል ።
ለድርቅ አፋጣኝ ምላሽ መሥጠት አስፈላጊ መሆኑን የሚያስገነዝገቡት የተመድ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ኃላፊ ስቴፈን አብራይን የኢትዮጵያ መንግሥት እኤአ በ2017 ለሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልገኛል ብሎ ላቀረበው ድጋፍ ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ምላሽ እንዲሠጥ ጥሪ አቅርበዋል ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረበው ሰነድ እንደሚያመለክተው በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ 5ነጥብ 6 ሚሊዮን ህዝብ ለአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ተረጂ መሆኑንና በአጠቃላይም 948 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግ ተመልክቷል ።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ በቆላማ የአርብቶ አደሩ አካባቢ መሆኑንና አስፈላጊውን እርዳታ ለተጎጂዎች በማድረስ የድርቁን ጉዳት መቀነስ እንደሚቻል ኦብራይን አስገንዝበዋል ። ( ምንጭ : ፋይናንሺያል ትሪቡን)