በአገር ውስጥ እየሠሩ የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን የመልካም አስተዳደር ማሳያ ሞዴል ሊሆኑ እንደሚገባቸው የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ ።
የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ዛዲግ አብርሃ ለመገናኛ ብዙሃን አመራሮች ፣ ጋዜጠኞችና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች በተዘጋጀው የአምስት ቀን የመልካም አስተዳደር ላይ የተኮረ ሥልጠና ላይ እንደገለጹት የመገናኛ ብዙሃን በአገሪቱ የመልካም አስተዳደር እንዲረጋጋጥ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይገባል ።
የመገናኛ ብዙሃን ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ በአገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን ነቅሰው ለማውጣት የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት በራሳቸው የመልካም አስተዳደርን ማስፈን እንደሚጠበቅባቸው አቶ ዛዲግ ተናግረዋል ።
በተለይም መገናኛ ብዙሃን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማጋለጥ ህብረተሰቡን በተገቢው መልክ ማወያያት ይገባቸዋል ያሉት አቶ ዛዲግ መገናኛ ብዙሃን መልካም አስተዳደር ላይ አስፈላጊውን ዘገባ በማቅረብ ተገቢውን ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ገልጸዋል ።
ሌላው የመገነኛብዙሃን በአገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች በወጡት ፖሊሲዎች ፣ አሠራሮችና ደንቦች አተገባባር ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በማሳየት ረገድም የመገናኛ ብዙሃን የሚጠበቅባቸውን ተግባራት ሊያከናውኑ እንደሚገባ አቶ ዛዲግ ጠቁመዋል ።
መንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ውስጥ የሚስተዋሉ የደሞዝ ማነስ ፣ የግብዓት እጥረቶች፣ የአቅምና ክህሎት ክፍተቶችን ለመሙሏት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አቶ ዛዲግ አስረድተዋል ።
የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ ስነ ምግባር የታነፀ በመሆን በመረጃ የተደገፈ የምርምራ ጋዜጠኝነትን ሥራን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተመልክቷል ።
የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ከመላ አገሪቱ ለተውጣጡ ከ200 ለሚበልጡ የመገናኛ ብዙሃን አመራሮች ፣ ጋዜጠኞችና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ያሳተፈ ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሥልጠና በዛሬው ዕለት ተጀምሯል ።