የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚንስትር ዶክተር ነገሪ ለንጮ በዛሬው ዕለት በሠጡት መግለጫ እንደገለጹት ከአራት ወራት በፊት በአገሪቱ ተግባራዊ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥና ልማት እንዲቀጥል አስችሏል ።
ዶክተር ነገሪ ሌጮ በመግለጫቸው በአገሪቱ አልፍ አልፎ መንግሥትንና ህዝብን የሚያጋጩ በራሪ ወረቀቶች የሚበተኑበት ሁኔታ ከመኖሩ በስተቀር በመላ አገሪቱ ሰላምና መረጋጋት የሚታይ መሆኑን ተናግረዋል ።
መንግሥት ለስድስት ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ እንዲሆን ያደረገው የተለያዩ የአግር ውስጥና የውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎች የማህበራዊ ሚዲያዎችንና የቴሌቪዥን ሥርጭቶችን በመጠቀም የአገሪቱን ወጣት ወደ ተሳሳተ መንገድ ለመምራት ሙከራ በማድረጋቸውን እንደሆነ ዶክተር ነገሪ አስረድተዋል ።
በአገሪቱ የሚገኙ ወጣቶች ማንኛውንም ጥያቄ ለመንግሥት በአግባቡ ማቅረብ እንደሚችሉ የተናገሩት ዶክተር ነገሪ ፀረ- ሰላም ኃይሎች የህብረተሰቡን ጥያቄዎች በመንተራስ ወደ አመጽ እንዲያመራና በመገፋፋታቸው የሰው ህይወት እንዲጠፋና የንብረት ውድመት እንዲፈጠር አድርገዋል ብለዋል ሚንስትሩ ።
እስካሁን ድረስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጻም ስኬታማ እንደነበርና በአገሪቱም የቱሪስትና ኢንቨስትመንት ፍሰት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።
እንደ ዶክተር ነገሪ ገለጻ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚነሳበት ጊዜ እስካሁን ያልተወሰነ መሆኑንና አዋጁ የሚነሳው የ6 ወሩ አፈጻጻም ተገምግሞ የህዝብ ተወካዮችን ምክር ቤት ውሳኔ ሲያስተላልፍ ነው ብለዋል ።
በሶማሌ ፣ በደቡብ ፣ እና በኦሮሚያ ክልል የድርቅ ሁኔታን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው ሚንስትሩ ድርቅ በተከሰተባቸው ሦስቱ ክልሎች የሰውና የእንስሳትን ህይወትን ለማትረፍ አስፈላጊው የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እየተከፋፈለ መሆኑን አመልክተዋል ።
ኢትዮጵያ ከግብጽና ከደቡብ ሱዳን ጋር ያላትን የፖለቲካ ግንኙነት በጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን የገለጹት ሚንስትሩ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚናፈሱት አሉታዊ ዘገባዎችን መሠረተ ቢስ መሆኑን ጠቁመዋል ።
በደቡብ ሱዳን የሚኖሩት የሙርሌ ጎሳዎች በጋምቤላ ክልል በመግባት አፍነው ከወሰዷቸው አጠቃላይ 150 ህጻናት መካከል እስካሁን ድረስ 91 የሚሆኑት መመለስ መቻላቸውንና በቀጣይ እንደዚህ አይነት ችግር እንዳይገጥም በአራት ቦታዎች ሚሊሺያና የመከላከያ ኃይል የጥበቃ ሥራ እንዲያከናውኑ መደረጉን ሚንስትሩ አብራርተዋል ።
በመጨረሻም በአገሪቱ በመካሄድ ላይ ያለው ህዝብን ያሳተፈ የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ጥሩ ውጤት እያስመዘገ መሆኑንና የህዳሴ ጉዞውን ለማሳካት እገዛ እንደሚኖረው ተግምቷል ።