የተሃድሶ ሠልጣኞች ህዝባቸውን መካስ ይገባቸዋል – ጽህፈት ቤቱ

የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ አካባቢያቸው የተመለሱት የተሃድሶ ሥልጠና ተመራቂዎች  ህዝባቸውን መካስ እንደሚጠበቅባቸው የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት አስታወቀ ።

ጽህፈት ቤቱ በላከው ሳምንታዊ መግለጫ እንዳመለከተው ከትናንት በስተያ 11ሺ 352 የሚሆኑ የሁለተኛ ዙር  የተሃድሶ ሠልጣኞች አስፈላጊው የግንዛቤ  ማስጨበጫ ሥልጠና ወስደው በመመረቃቸው ከህብረተሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ተደርጓል  

የሁለተኛ ዙር ሠልጣኞቹ በአራት ማዕከላት ለ20ቀናት በህገ መንግሥቱ፣ ህገመንግሥታዊ ሥርዓቱ፣  አገሪቱ ስላለፈችበት  ሂደትና የወደፊቱ አቅጣጫ  ላይ የነበራቸውን  ግንዛቤ የሚያሳድግ ሥልጠና ተሠጥቷል ።        

በመጀመሪያው  ዙር የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው  የተመረቁት  9ሺ 800 ያህል ሠልጣኞች ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው ገንቢ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን የጠቆመው መግለጫው  የሁለተኛው ዙር ተመራቂዎችም ተመሳሳይ ገንቢ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል ብሏል ።

ሠልጣኞች   ወደ መደበኛ ሥራዎቻቸውና ህይወታቸው በሚመለሱበት ጊዜ የሚመለካታቸው አካላት በሙሉ  ተገቢውን ትብብር እንደሚያደርጉላቸው  የጽህፈት ቤቱ መግለጫው አትቷል ።      

ሠልጣኞች  ወደ ህብረተሰቡ በሚቀላቀሉበት ወቅት ያገኙትን ሥልጠና ተጠቅመው በልማቱ ውስጥ  የተሻለ ተሳትፎ በማድረግ ፤ ሌሎች የግንዛቤ እጥረት ያለባቸውን ማስተማርናማረም እንዳለባቸው በመግለጫው ተመልክቷል ።