ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከል የተጀመረው ቅንጅታዊ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት— አቶ ከበደ ጫኔ

በአገሪቱ የሚታየውን ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከል የተጀመረው ቅንጅታዊ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ አስታወቁ፡፡

10ኛው  ሀገር አቀፍ የግብር እና ቀረጥ ሳምንት ትናንት በጅግጅጋ ከተማ በፓናል ውይይት መከበር ጀምሯል፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ  በውይይቱ ላይ እንደገለፁት ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የአገር ኢኮኖሚን ይጎዳል፡፡

ባለፉት ዓመታት በተለይ የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ህብረተሰብ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከል ባካሄደው ጥረት በመጠኑም ቢሆን ህጋዊ የግብይት ስርዓት እንዲይዝ ማገዙን ገልፀዋል፡፡

አሁንም ግን የኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴ እንዳልቆመ የጠቆሙት  ሚኒስትሩ "በህገ ወጥ መንገድ ወደ መሃል አገር የሚገቡ ሸቀጦች የአዲስ አበባ ገበያን እያጥለቀለቁት ነው "ብለዋል፡፡

ይህ ደግሞ በህጋዊ መንገድ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘውን የንግድ ህብረተሰብ እየጐዳው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

እንዲሁም ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በአግባቡ ለህብረተሰቡ እየደረሰ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

በተለይ ለኦሮሚያ ክልል ከፊል ዞኖች የተፈቀዱ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በኢትዮዽያ ሶማሌ ክልል ከተሞች ሲሸጥ መገኘቱን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡

ህገ – ወጥ ነጋዴዎቹ በክልሉ ነዋሪዎች ስም ለማህበራት የተሰጠውን ፈቃድ ከማህበራቱ በመከራየት እየተጠቀሙ  መሆናቸውን ጠቁመው ይህም በየክልሎቹ የሚገኙ ፈቃድ ሰጪ መስሪያ ቤቶች ክትትል እንዳላደረጉ እንደሚያመላክት ተናግረዋል፡፡

ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከልና የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ በየደረጃው የሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት የተናበበ እቅድ በማዘጋጀት የጀመሩትን ቅንጅታዊ ስራ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሀሙድ ከቀረጥ ነፃ መፈቀዱ የህብረተሰቡን ችግሮች እንዲፈቱ እያገዘ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

 

አቅርቦቱን በተመለከተም ለተፈቀደላቸው አርብቶ አደሮች በጊዜና በአግባቡ እንዲቀርብ በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት ቀጣይ ክትትል እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

በክልሉ የጠረፍ አካባቢ ነዋሪዎችን ወደ ህጋዊ ንግድ እንቅስቃሴ እንዲገቡ የሚደርግ አሰራር አለመኖሩን የገለፁት ርእሰ መስተዳድሩ የፌዴራል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ከንግድ ሚኒስትር ጋር በመነጋገር ችግሩን መፍታት እንደሚገባው ገልፀዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የክልል ገቢዎች ተወካዮች የክልሉ ጠረፋማ ወረዳዎች አመራሮች የባለስልጣኑ አመራሮችና ሰራተኞች ተሳትፈዋል፡፡

የግብር እና ቀረጥ ሳምንት በፓናል ውይይቶች፣ በፎቶ እግዚብሽን እና በእግር ጉዞ መርሃ – ግብሮች እስከ የካቲት 1 ቀን 2009 ይከበራል፡፡ (ምንጭ – ኢዜአ)