በአገሪቱ እየሠሩ የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን ግጭትን በመከላከል ረገድ ትኩረት ሠጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ ተመለከተ ።
የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ለመገናኛ ብዙሃንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች፣ አመራሮች እየሠጠ ባለው ሥልጠና የመገናኛ ብዙሃንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በማህበረሰብ ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችንና ቅራኔዎችን በመከላከል በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም መስፈን የበኩላቸውን ሚና ሊጫወቱ ይገባል ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የውጭ ግንኙነት፣ ትብብርና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ዘነበ በየነ በሥልጠናው ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ እንደገለጹት በአገሪቱ የትኛውም አካባቢ ግጭት በሚፈጠርበት ጊዜ የግጭቱን መንስኤ፣ ተዋናዮችንና የሚያመጣውን ውጤት ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚጠበቅበባቸውን ሙያዊ ግዴታ መወጣት ይገባቸዋል ።
የመገናኛ ብዙሃንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በግጭት ወቅት ከስሜታዊነት በራቀ ሁኔታ ለህብረተሰቡ ተገቢውን መረጃ ማቅረብ እንደሚገባቸው የጠቆሙት ዶክተር ዘነበ ሙያው በሚያዘው መሠረት ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የበኩላቸውን ሚና የመጫወት ኃላፊነት አለባቸው ።
ለአገሪቱ ለሰላም ዘብ መቆም የሁሉም ዜጋ ግዴታ መሆኑን ያብራሩት ዶክተር ዘነበ በአገሪቱ የተረጋገጠውን ዘላቂ ሰላም ጠብቆ ለማቆየት የሁሉም ግዴታ እንደሆነ አስረድተዋል ።
የመገናኛ ብዙሃን በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ ግጭቶችን አስቀድሞ ለመከላከል ህብረተሰቡና መንግሥት በግልጽ ውይይት እንዲያደርጉ ድልድይ በመሆን አስተማማኝ ሰላም እንዲጎለብትና ልማቱ እንዲቀጥል ጥረት ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል ዶክተር ዘነበ ።
የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በልማታዊ ዴሞክራሲ ፣ በግጭት ምንነትና በብሔራዊ መግባባት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለመገናኛ ብዙሃንና ለህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችና አመራሮች ለአምስት ቀናት ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና በዛሬው ዕለት ይጠናቀቃል ።