ኢህአዴግን ጨምሮ የአገሪቱ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክርና ድርድር የሚመሩበት ስርዓት መነሻ ሃሳብ በዝርዝር አቅርበዋል ፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የመንግስት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ዛሬ የተገኙት 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲሆኑ፤ የመነሻ ሃሳባቸውን ያቀረቡት ግን 20 የፖለቲካ ፓርቲዎች መሆናቸውን ነው የተመለከተው ፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጥር 10/2009 ዓመተ ምህረት ዝርዝር መነሻ ሃሳቦች ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ጽሕፈት ቤት ያስገቡትን በ12 ዋና ዋና አጀንዳዎች ቀርቧል፡፡
ከነዚህም ውስጥ የድርድርና የክርክር ዓላማ፣የድርድርና የክርክር ተሳታፊ ፓርቲዎች፣ የድርድርና የክርክር ፎረም አባላት የፓርቲ ተወካዮች ብዛት የሚሉ ይገኙበታል ፡፡
እንደዚሁም ምልአተ ጉባኤና ውሳኔ አሰጣጥ ፣አጀንዳ አቀራረብና የአጀንዳ ማቅረቢያ ጊዜ ፣የሚድያ አጠቃቀም እና የንግግርና የተናጋሪዎች አሰያየም የሚሉት ነጥቦች ተካተዋል ፡፡
በተጨማሪም የድርድር አመራር ፣የጋራ ፎረም አባላትና ታዛቢዎች በተመለከተ ፣የስነ ምግባርና ዲሲፕሊን ፣የአስተዳደርና ሎጂስቲክስ እና የስብሰባ ቦታ በሚመለከቱ አጀንዳዎች ላይ ዝርዝር ሃሳቦች በንባብ ቀርበዋል ፡፡
ከዚህም በኋላ ተሰብሳቢዎቹ በዲሞክራሲያዊ አገባብ አምስት አባላት ያሉት አንድ ኮሚቴ መርጠው ለመገናኛ ብዙኋን መግለጫ እንዲሰጡ አድርገዋል ፡፡
የተመረጡት ኮሚቴ አባላቱም በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫና ማብራሪያ አጀንዳዎቹ ላይ በማተኮር ዛሬ የተካሄደውን ስብሰባ ብቻ ኢህአዴግ እንዲመራው ፓርቲዎቹ በሙሉ ድምጽ በተስማሙበት መሰረት መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
ፖለቲካ ፓርቲዎቹ የሚመሩበት ደንብ ለማዘጋጀት የወሰኑ ሲሆን ፤ ፓርቲዎቹ ረቂቅ ደንቡን የሚያዘጋጁ ሰባት አባላት መመረጣቸውን አስታውቋል ፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የካቲት 17/2009 ዓመተ ምህረት ዳግም ለመገናኘት መወሰናቸውን ኮሚቴው ጠቁሟል ፡፡
በዚሁም ጊዜ ፓርቲዎቹ በረቂቅ ደንቡ ላይ በሚገባ ከተወያዩበት በኋላ በአፋጣኝ ወደ ውይይትና ድርድር ለመግባት መግባባታቸውንም ኮሚቴው ገልጸዋል ፡፡
በቀጣይ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አንድ በሚያደርጓቸው አጀንዳዎች ላይ በመስማማት በልዩነታቸው ላይ ደግሞ በመወያየት በጋራ እንደሚቀጥሉ አመልክቷል ፡፡
ኢህአዴግና ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ቀጣይ ክርክርና ድርድር የሚመራው አካልም በረቂቅ ደንቡ ላይ በጥልቀት ከተወያዩ በኋላ የሚወሰን መሆኑን ኮሚቴው አስታውቀዋል ፡፡
የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት እና የመላ ኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ለጊዜው ባልታወቀ ምክንያት የመነሻ ሃሳባቸው እንዳላቀረቡ ነው ኮሚቴው የገለጸው ፡፡
የሚድያ አጠቃቀም ኮሚቴ ያስፈለገበት ምክንያት ደግሞ በተለያዩ መገናኛ ብዙኋን የተዛባ መረጃ እየተሰራጨ በመሆኑ ይህንን ለማስወገድና ትክክለኛ መረጃ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ እንደሆነ ኮሚቴው ማስታወቁን ዋልታ ዘግቧል ፡፡