በኦሮሚያ በኪራይ ሰብሳቢነት የተጠረጠሩ አመራሮች ላይ ማስረጃ እየተሰበሰበ ነው

በኦሮሚያ ክልል በተካሄደው ጥልቅ ተሃድሶ በኪራይ ሰብሳቢነት የተጠረጠሩ ከ3 ሺህ 400 በላይ አመራሮችን በሕግ ለመጠየቅ ማስረጃ እየተሰበሰበ መሆኑን የክልሉ ኮምኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በክልሉ የተካሄደውን የመጀመሪያ ምዕራፍ ጥልቅ የተሃድሶ ጉዞ መጠናቀቅ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤በጥልቅ ተሃድሶ ግምገማው ሕዝቡን ያማረሩና ለቅሬታ የዳረጉ ዋና ዋና ችግሮችን መለየት ተችሏል ።

በጥልቅ ተሃድሶው የተነሱ ችግሮች ባለቤት እንዲኖራቸው ለማድረግ በተለዩ አካላት ላይ ፖለቲካዊና ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ማስረጃዎች እየተሰባሰቡ መሆኑን ገልጸዋል።

በተወሰዱ ፖለቲካዊ እርምጃዎች ሁለት አመራሮች ከስራ አስፈጻሚ ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲሸጋሸጉ የተወሰነ ሲሆን ሶስት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መታገዳቸውን ገልጸዋል።

ከክልል እስከ ወረዳ ባለው መዋቅር 4 ሺህ 660 አመራሮች ከኃላፊነታቸው የተነሱ ሲሆን በቀበሌ ደረጃም ከ13 ሺህ 500 በላይ አመራሮች እንዲነሱ ተደርጓል ነው ያሉት ።

የአመራር አባላቱ የታገዱት በአቅም ማነስ፣ በኪራይ ሰብሳቢነት፣ በስነ ምግባር ጉድለትና በሌሎች ምክንያቶች መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በሕግ አግባብ በተወሰዱ እርምጃዎችም ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ 946 አመራሮች በኪራይ ሰብሳቢነት ተጠርጥረው ማስረጃ እየተሰባሰበ መሆኑንና 260 የሚሆኑት በቁጥጥር ስር ውለው ክስ እንደተመሰረተባቸው አስታውቀዋል።

በቀበሌ ደረጃ የተጠረጠሩ 2 ሺህ 470 የአመራር አባላትን ለሕግ ለማቅረብ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ፣ አራት ተሽከርካሪዎች፣ 40 መኖሪያ ቤቶችና ከ244 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ የከተማ መሬት በህግ እገዳ ተጥሎባቸው ተጨማሪ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የክልሉ ሕዝብ ፍላጎትና አቅርቦት ባለመጣጣሙ ከፍተኛ ቅሬታ ተፈጥሮ ነበር ነው ያሉት ።

በመሆኑም የክልሉ መንግስት ሌሎች ከመልካም አስተዳደር እጦት ጋር ተያይዘው ሲነሱ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ወደ ጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ ገብቷል ብለዋል ።

በጥልቅ ተሃድሶው ከማዕከላዊ ኮሚቴ እስከ ቀበሌ ባለው እርከን ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ተካተው በድምሩ ከ6 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተሳትፎበታል መሳተፉን ጠቁመዋል ።

በመጨረሻም ከክልሉ 20 ዞኖችና 10 ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 20 ሺህ ሰዎች የጥልቅ ተሃድሶ ጉዞው ሂደት ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል ።

ሕብረተሰቡ በተለይም የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭና ተግባራት በሆኑት የመሬት አስተዳደር፣ የግዥና ኮንትራት አስተዳርና ገቢ አሰባሰብ ዙሪያ ከፍተኛ ችግር መኖሩን አንስተዋል።

የስርዓቱ አደጋ የሆኑት ጠባብነት፣ አክራሪነትና ጎሰኝነት በአመለካከትና በተግባር መኖራቸውንም ገልጸዋል።

"በተሃድሶ ሂደቱ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር ትክከለኛ መስመር መሆኑ መግባባት ላይ ተደርሷል" ነው ያሉት አቶ አዲሱ።

አመራሩ በበኩሉ ችግሮቹን ለማስወገድና የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ቃል የገባበት ነው ብለዋል።

በተለይም በፍትህ ዘርፍ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማስወገድ፤ የመንግስት ሰራተኛውም በለውጥ መሳሪያዎች የተቃኘ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ የሆኑበት እንደሆነም ገልጸዋል።

በአጠቃላይ ከክልሉ ካቢኔ ጀምሮ በዞንና በከተማ አስተዳደሮች ደረጃ የአመራር ለውጥ መደረጉን ነው ያስታወቁት።

"ህዝቡ ጥልቅ ተሃድሶው በሂደት ላይ መሆኑን ታሳቢ ማድረግ አለበት" ያሉት ኃላፊው የክልሉ ሕዝብ ለተሃድሶው ስኬት ያበረከተው አስተዋጽኦ የሚያስመሰግነው መሆኑን አክለዋል-(ኢዜአ) ።