የደቡብ ክልል ባካሄደው የጥልቅ ተሃዲሶ ግምገማ 20ሺህ 173 ከፍተኛ አመራሮችን ከኃላፊነት ማንሳቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ የክልሉ ምክር ቤት አራተኛ መደበኛ ጉባኤውን ትናንት ሲጀመር እንደገለጹት ፤ ባለፉት ስድስት ወራት የጥልቅ ተሃድሶ መድረኮችንና የትራስፎርሜሽን አጀንዳዎችን ስኬታማ ለማድረግ የሚያስችል ርብርብ ተደርጓል ።
በሂደቱ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ 496 ሺህ 311 አመራሮች እንዲያልፉ ተደርጎ 1ሺ 920 ከፍተኛ አመራሮችና 18 ሺህ 253 መካከለኛ አመራሮች ከኃላፊነት እንዲነሱ መደረጉን አስታውቀዋል።
የክልሉ መንግስት የ15 ዓመታት የተሃድሶ ጉዞውን ከከፍተኛ አመራር በመጀመር እስከ ህዝቡ የዘለቀ በጥልቀት የመታደስ ትግል መደረጉንም ጠቅሰዋል።
የህዝብ ጥያቄዎችን በመለየት በህዝብ የተደራጀ ተሳትፎ ለመፍታት በተደረገው ጥረትም የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸው አመልክተል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ባቀረቡት ሪፖርት በህብረተሰቡ ውስጥ ቅሬታና የመልካም አስተዳደር ቅሬታ እየፈጠሩ ባሉ የመሬት አስተዳደር ሙያተኞችና ኃላፊዎች ፣ የህገ ወጥ የትምህርት ማስረጃ በተጠቀሙ ፣ የተመዘበረ የመንግስትና የህዝብ ገንዘብ ለግላቸው ባዋሉ አካላት ላይ እርምጃ ተወስዷል።
ጉባኤው በትናንትናው ውሎ የርዕሰ መስተዳደሩን ሪፖርት ካደመጠ በኃላ በግብርው ዘርፍ ፣በገቢ አሰባሰብና በከተሞች የመልካም አስተዳደር ላይ በተገኙ ስኬቶችና ተግዳሮቶች ላይ ውይይት ማድረግ ጀምሯል-(የደቡብ ሬድዮና ቴሌቭዥን ድርጅት)