የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ጉባኤበስነ ምግባር ጉድለት ምክንያት 18 ዳኞችን እንዲነሱ ሲያደርግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ለከፍተኛ ፍርድ ቤትና ለወረዳ ፍርድ ቤቶች የ116 ዳኞችን ሹመትን አጽድቋል ፡፡
ምክርቤቱ የተሰጣቸውን የዳኝነት ስልጣን ለግል ጥቅም በማዋልና በስነ ምግባር ጉድለት ምክንያት 18 ዳኞችን እንዲነሱ ሲያደርግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ለከፍተኛ ፍርድ ቤትና ለወረዳ ፍርድ ቤቶች የ116 ዳኞችን ሹመት በማጽደቅ ዛሬ ጉባኤውን ዛሬ አጠናቋል ፡፡
እንደዚሁም ምክር ቤቱ የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር የስራ ቆይታቸው በማብቃቱና የስራ መልቀቂያ በማስገባታቸው በቦታቸው አቶ ተስፋዬ ታፈሰን ዋና ኦዲተር በማድረግ ምክር ቤቱ ሾሟል፡፡
የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የቦርድ አባል በነበሩት ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን ምትክ አቶ ሰለሞን ኃይሉ እንዲተኩ ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡
የሃድያ ብሔረሰብን ወክለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወካይ እንዲሆኑ አቶ ስንታየው ወልደሚካኤልን ምክር ቤቱ ወክሏል፡፡
ጉባኤው የታክስ አስተዳደር፣ የከተሞች አስተዳደርና የገቢ ግብር አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል ፡፡
የክልሉ ታክስ አስተዳደር ስርዓት ራሱን ችሎ የበለጠ ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆን የታክስ አስተዳደር አዋጁ መውጣቱ ተገልጿል፡፡
አዋጁ በታክስ ህጎች አተረጓጎም ረገድ በታክስ አስተዳደሩ ውስጥ በሚፈጠር ልዩነት ምክንያት ታክስ ከፋዩ ሲያጋጥመው የነበረውን እንግልት በማስቀረት ወጥነት ያለው እንዲሆን ያስችላል፡፡
የከተሞች አስተዳደር አዋጅ ደግሞ በክልሉ መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ሁሉን አቀፍ ልማት በማረጋገጥ ከተሞች የምርት የአገልግሎትና የገበያ ማዕከላት ሆነው የክልሉን ኢንዱስትሪ ልማት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያችል ተመልክቷል፡፡
እንዲሁም የገቢ ግብር አዋጅ የግብር አከፋፈል ስርዓቱ ፍትሀዊነት ያለው እንዲሆንና ግብር የማይከፈልባቸውን ገቢዎች በግብር መረብ ውስጥ ለማስገባት እንደሚያስችል በጸደቀው አዋጅ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡
የክልሉ ኢኮኖሚ ዕድገት ከደረሰበት ደረጃ ጋር የተጣጣመና ኢኮኖሚውን የሚያግዝ ዘመናዊና ቀልጣፋ የግብር ስርዓት ለመዘርጋት በማስፈለጉ አዋጁ መውጣቱ ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም ለመምህራን የደሞዘ ጭማሪ በክልል ማዕከል ለሚገኙ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ፣ለተለያዩ ኮሌጆችና ሌሎችን ተግባራት የሚውል ከአንድ ቢሊዮን 682 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት በማጽደቅ ጉባኤው ተጠናቋል-(ኢዜአ) ፡፡